አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሳውላ ካምፓስ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን በቅድመ ምረቃ 193 እና በ2ኛ ዲግሪ 6 በድምሩ 199 ተማሪዎችን ሰኔ 26/2014 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 89ኙ ሴቶች ናቸው፡፡

የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራል፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባልና የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ፈጠነ ተሾመ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልእክት ጥራት ያለው ትምህርትና ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በልዩነት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ከተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ጠቅሰው መንግሥት የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሻሻል በሚሠራቸው ሥራዎች ዩኒቨርሲቲው የራሱን አሻራ ማሳረፍ ይገባዋል ብለዋል፡፡ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ለስኬት የበቁ ተመራቂዎች ችግር ፈቺ ሙያተኞችና ቀና አገልጋዮች በመሆን ለሀገራቸው የተማረ የሰው ኃይል ፍላጎት ምላሽ እንዲሰጡም አሳስበዋል፡፡   ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና መልካም የማኅበረሰብ እሴቶች የሚገኙባት ሀገራችን ኢትዮጵያን ሰላሟን ጠብቆ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበረሰብና ምሁራን ድርሻቸው የጎላ በመሆኑ ምሩቃን ከዩኒቨርሲቲው በገበያችሁት ዕውቀትና ክሂሎት በየተሰማራችሁበት መስክ ሁሉ ሕዝባችሁንና ሀገራችሁን ልታገለግሉ ይገባል ብለዋል፡፡

በም/ፕሬዝደንት ማዕረግ የሳውላ ካምፓስ ኃላፊ አቶ ገብረመድኅን ጫሜኖ ካምፓሱ የሚያስመርቃቸው ተማሪዎች በዕውቀትና በሥነ-ምግባር ታንጸው ኃላፊነትን የሚቀበሉ ብቁ ዜጎች እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ለሴቶች እና ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር ላለባቸው ተማሪዎች ልዩ ትኩረትና እገዛ ስለመደረጉ ከዕለቱ ተመራቂዎች መካከል በሁሉም ት/ክፍሎች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ሴቶች መሆናቸው ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን /አልሙናይ/ ማኅበር ፕሬዝደንት አቶ ኤርሚያስ ዓለሙ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት በጽናት አልፈው ለምረቃ እለታቸው በመድረሳቸው ተመራቂዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ ምሩቃን ከሌሎች የአልሙናይ አባላት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት የተማሩበትን ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር፣ በማኅበረሰብ አገልግሎትና በተለየዩ ጉዳዮች ለመደገፍ በዩኒቨርሲቲው ድረ-ገጽ፣ በአልሙናይ ቴሌግራም ቻናል እና ፌስቡክ ፎርም በመሙላት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አልሙናይ ማኅበር አባል እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ተማሪ ገብርኤላ ሀብታሙ 3.999 እና 54 A+፣ ተማሪ እድላዊት በረከት 3.99 እና 35 A+፣ ተማሪ ፋሲካ ቶሎሳ 3.98 እና 54 A+፣ ተማሪ ቤተልሔም ዓባይነህ 3.92 እንዲሁም ተማሪ ምሥጢር ተክሉ 3.88 በማምጣት ከየትምህርት ክፍሎቻቸው ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግበው ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ገብርኤላ ሀብታሙ የካምፓሱን ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገቧ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች። ተመራቂ ገብርኤላ ለዚህ ስኬት በመብቃቷ የተሰማትን ደስታ ገልጻ በተመረቅሁበት መስክ ያስተማረኝን ማኅበረሰብ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ብላለች፡፡

ሳውላ ካምፓስ በትምህርት ዘመኑ በቅድመ ምረቃ 2,467 እና በድኅረ ምረቃ 95 በአጠቃላይ 2,562 ተማሪዎችን በማስተማር ላይ ሲሆን የዘንድሮዎችን ጨምሮ በ5 ዙሮች 1,497 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት