የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ከ15 ዓመት በታች በሁለቱም ፆታዎች የፓይለት ፕሮጀክት ምዘና ውድድር ከሐምሌ 17-ነሐሴ 1/2014 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ዳይሬክተርና የታዳጊ ወንዶች ቡድን አሠልጣኝ አቶ አሰግድ ከተማ ዩኒቨርሲቲው ከ15 ዓመት በታች ወንዶችንና ሴቶችን በፓይለት እግር ኳስ ፕሮጀክት ለ3 ዓመታት ሲያሠለጥን መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲው፣ በትምህርት ሚኒስቴርና በእግር ኳስ ፌዴሬሽን የጋራ ስምምነት በ2012 ዓ/ም የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው በሳምንት ሦስት ቀን እንዲሁም በቀን ለ2 ሰዓታት ሳይንሳዊ መርሆዎችን ጠብቆ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

በፕሮጀክቱ የታቀፉት ታዳጊ ወንዶች በአርባ ምንጭ ከተማ ከዕድሜ አቻዎቻቸው ጋር ከተደረጉ ጨዋታዎች አብዛኛዎቹን በአሸናፊነት ማጠናቀቃቸውን እንዲሁም 4 ታዳጊዎች ለተለያዩ ሀገራዊ ክለቦች ተመርጠው አንዱ ወደ ክለቡ ሲቀላቀል 3ቱ ጥሪ እየተጠባበቁ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለስፖርተኞች የሜዳ፣ የመኝታ፣ የምግብ፣ የስፖርት ትጥቅና ሌሎች ድጋፎች በመስጠት ለውድድሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን በተለይም የአርባ ምንጭ ከተማ ሕዝብ ለስፖርት ቅርብና ለእግር ኳስ የተለየ ስሜት ያለው ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በከተማዋ በየሰፈሩ የታዳጊ ሕፃናት ፕሮጀክቶች መኖራቸውና የታዳጊ ቤተሰቦችም በፈቃደኝነት ልጆቻቸውን ለፕሮጀክቶች እየሰጡ መሆኑ ለወደ ፊቱ የእግር ኳስ ስፖርት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንደ ዩኒቨርሲቲ በ2015 በጀት ዓመት ከእግር ኳስ በተጨማሪ በሜዳ ቴኒስ፣ በባድሜንተን እና በውሃ ስፖርት ዘርፎች በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

በውድድሩ የታዳጊ ሴቶች ቡድን በግማሽ ፍጻሜ የሲዳማ ታዳጊ ሴቶች ቡድንን 2 ለ 0 በማሸነፍ እንዲሁም በፍጻሜው የድሬዳዋ ከተማ ታዳጊ ሴቶች ቡድንን 1 ለ 0 በመርታት የውድድሩ ሻምፒዮን ሆኖ ዋንጫውን አንስቷል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የታዳጊ ወንዶች ፕሮጀክት ቡድንም ከአዲስ አበባ ታዳጊ ወንዶች ፕሮጀክት ቡድን ጋር ለደረጃ ባደረገው ጨዋታ 3 ለ 0 በመርታት 3ኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡

በፓይለት ፕሮጀክት ውድድሩ የዩኒቨርሲቲው ቡድኖች ውጤታማ ነበሩ ያሉት በዩኒቨርሲቲው የስፖርት ሳይንስ መምህርና የታዳጊ ሴቶች አሠልጣኝ ኢንስትራክተር ሙሉጌታ ደበበ በኮከብ አሠልጣኝነት ሜዳሊያ መሸለማቸው የበለጠ እንዲሠሩ ያነሳሳቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት