በጫሞ ሐይቅ ተፋሰስ ላይ ለመተግበር የታሰበውን የአነስተኛ መሬትና የውሃ አያያዝ ሥራዎች ፕሮጀክት በተመለከተ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣ ከኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን እና ከጋሞ ዞን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ነሐሴ 5/2014 ዓ/ም ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት ብርቅዬ የተፈጥሮ ሀብት የሆኑት አባያና ጫሞ ሐይቆች የተፈጥሮ ሚዛንን ከማስጠበቅ ባሻገር ለሀገርም ሆነ ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ የሀብቶቹን ውበትና ደኅንነት ጠብቆ በዘላቂነት መከታተል አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ በዚህ ረገድ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ነው ብለዋል፡፡

የኃ/ማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን የአካባቢ ጥበቃ ኃላፊ ዶ/ር ዓለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው በጋሞ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጥሮ ሀብት መራቆት ምክንያት እየተፈጠረ ያለውን አየር ብክለት ለማስቆም በፕሮጀክቱ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ የአቅም ውስንነት ያለባቸው ሴቶችን በማደራጀት በተራቆቱ አካባቢዎች ችግኝ በመትከል እንዲሸፈን እየተደረገ ሲሆን የማኅበሩ አባላትም ዘላቂ ገቢ በማግኘት ሕይወታቸውን በመቀየር ላይ ናቸው፡፡ የጫሞ ሐይቅ አካባቢን ለመቀየር ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎቹን ተጠቅሞ የመፍትሔ ሃሳቦችን ማቅረብ እንደሚገባውና ሌሎች ባለድርሻ አካላትና ማኅበረሰቡም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

የAMU-IUC ፕሮግራም ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በብዝሃ ሕይወትና አጠቃላይ የሰዎችን ሕይወት ለማሻሻል የሚሠራ በመሆኑ ሀገራዊና አህጉራዊ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡ በገረሴ አካባቢ ጌጃ ደንና በጫሞ ሐይቅ ዙሪያ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ክፍተት ለመሸፈን፣ ዘላቂ ልማት ለማምጣትና ከሰው ንክኪ ለመከላከል አስፈላጊ ሥራዎችን ወደ መሬት ለማውረድ ወርክሾፑ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

 

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት