የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የ2015 በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ ቁልፍ የውጤት አመላካች (KPI) ላይ ነሐሴ 20/2014 ዓ/ም ከዩኒቨርሲቲው ም/ፕሬዝደንቶች ጋር የውል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በውል ስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት የዩኒቨርሲቲው የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ የጸደቀ ሲሆን የም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤቶች የዕቅድ ቁልፍ ተግባራትም በዚሁ ዕቅድ ላይ ተመሥርተው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ በቀጣይ ዕቅዱን እስከ ባለሙያዎች ድረስ በማውረድና ውል በመፈራረም እንደሚሠራና በግለሰብ ደረጃ የሥራ አፈፃፀም ምዘና ሲደረግም በዚሁ መሠረት ሊሆን እንደሚገባ እንዲሁም የተሻለ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ሠራተኞችን ማበረታታትና መሸለም እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ላይ ኢንደስትሪዎችና ሴክተር መሥሪያ ቤቶችን ማሳተፍ፣ አዲስ የሚከፈቱ ፕሮግራሞች የዕውቅና ፈቃድ እንዲሁም ነባር ፕሮግራሞች የዕውቅና ፈቃድ እድሳት በሚመለከተው አካል ማሰጠት፣ በትምህርት ሚኒስቴር የሚሰጠውን የመውጫ ፈተና ተግባራዊ ማድረግ፣ ለመውጫ ፈተና ተማሪዎችን በሚገባ ማዘጋጀትና የማለፍ ምጣኔን 100% ማድረስ፣ 40 ተማሪዎች በተመረጡ የውጭ ተቋማት የአጫጭር ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ፣ በሀገር ውስጥ የ3ኛ ዲግሪ ትምህርት እድል ለ40 መምህራንና በውጭ ሀገር ለ20 መምህራን መስጠት፣ ለ500 አመራሮች፣ መምህራን እና የICT ባለሙያዎች መሠረታዊ የኮምፒውተር አጠቃቀም (Digital Literacy) ሠልጥነው የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ ማድረግ እንዲሁም የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ቁጥር ከ26 ወደ 33 ማድረስ በአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ስር ከታቀዱ ዐበይት ተግባራት መካከል ውስጥ ይገኙበታል፡፡

በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ከታቀዱና በውል ስምምነት ሰነድ ውስጥ ከተካተቱ ዋነኛ ተግባራት መካከል 22 አዳዲስ ግራንድ ምርምሮች፣ 12 ነባር ግራንድ ምርምሮችና 5 መሠረታዊ ምርምሮች ማካሄድ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጆርናሎችን ቁጥር ከ5 ወደ 6 ማድረስና 2ቱ ዕውቅና (Accreditation) እንዲያገኙ ማስደረግ፣ 50 የምርምር ውጤቶችን በሀገር ውስጥ እንዲሁም 200 የምርምር ውጤቶችን በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ማሳተም፣ በተቋሙ ከሚካሄዱ ምርምሮች ውስጥ 4 በመቶዎቹ በሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ፣ ለ6,100 የማኅበረሰብ ክፍሎች ነፃ የሕግ ጥብቅና፣ ምክር አገልግሎትና ሰነድ ዝግጅት አገልግሎቶችን መስጠት፣ 8 ችግር ፈቺ የማኅበረሰብ ፕሮጀክቶችን መተግበር፣ 1 የተጎዳ ተፋሰስ በመለየት ማኅበረሰቡን በማሳተፍ መልሶ ማልማትና ቀደም ሲል የተጀመሩ 2 የተፋሰስ ጥበቃና ልማት ሥራዎችን አፈጻጸም ወደ 75 በመቶ ማሳደግ፣ በአርባ ምንጭ ከተማ የሚመሠረተውን የልኅቀት አዳሪ ት/ቤት መደገፍ፣ 11 የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማሸጋገር እንዲሁም 4 ቴክኖሎጂዎችን በመለየት አምሳያቸው/Prototype/ እንዲሠራ ዝግጁ ማድረግ ይጠቀሳሉ፡፡

በሂደት ላይ ያሉ 13 ነባር የግንባታ ፕሮጀክቶች መሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲውሉ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት፣ ስታንዳርድን መሠረት በማድረግ ምቹ የመሥሪያ አካባቢ መፍጠር፣ ለትምህርት፣ ለምርምርና ለአስተዳደር ሥራዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማሟላት፣ ተቋሙን የከፍተኛ ፍጥነትና ተመጣጣኝ ብሮድባንድ ኢንተርኔት ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ፣ ዋናው ግቢን ጨምሮ በየካምፓሶች የመንገድ መብራት ፖል ተከላና ሙሉ ዝርጋታ እንዲሠራ ማድረግ፣ የዩኒቨርሲቲው ገቢ በመደበኛ በጀት የመሰብሰብ አቅም አሁን ካለበት ደረጃ 9 በመቶ ማሳደግ፣ ለ263 የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ሠራተኞችና ቤተሰቦች የቴክኒኪና ሙያ፣ የመጀመሪያና የ2ኛ ዲግሪ ነፃ የትምህርት እድል መስጠት፣ በአስተዳደር ዘርፍ የሥራ መደቦች የሰው ኃይል ማሟላትና የሠራተኞችን ቁጥር ከ4,973 ወደ 5,522 ማሳደግ፣ በአካዳሚክ ዘርፍ የሰው ኃይልን በቅጥርና በደረጃ እድገት ማሟላት፣ በተለያየ ደረጃ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ተሸከርካሪዎችና ሌሎች መጓጓዣዎች መረጃ በመለየት ማሳደስና ለአገልግሎት ብቁ ማድረግና የደንብ ልብስ ለሚያስፈልጋቸው የአስተዳደር ሠራተኞች አቅርቦ አፈጻጸሙን ማረጋገጥ በአስተዳደር ጉዳዮች ዘርፍ ለመፈጸም ውል ከተገቡ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት፣ ም/ፕሬዝደንቶች፣ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተሮች፣ ዳይሬክተሮችና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት