የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ መስክ በጤና ኢንፎርማቲክስ የ2ኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ለመክፈት መስከረም 6/2015 ዓ/ም የሥርዓተ ትምህርት የውጭ ግምገማ አካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ 

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ተወካይና የም/ፕሬዝደንቱ ልዩ አማካሪ ዶ/ር ነጂብ መሐመድ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ75 የመጀመሪያ፣ በ134 የ2ኛና በ26 የ3ኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች በርካታ ተማሪዎችን እያሠለጠነ መሆኑን ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ምርምር ተኮር የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን በመክፈትና ብቁ ሙያተኞችን በማፍራት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ በኮሌጁ በጤና ኢንፎርማቲክስ የ2ኛ ዲግሪ ፕሮግራም ለመክፈት ሥርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱ የዩኒቨርሲቲው ዕቅድና ተልዕኮ እንዲሳካ የራሱ ሚና አለው ያሉት ዶ/ር ነጂብ በግምገማው የሚነሱ አስተያየቶች ለመርሃ ግብሩ ጥራት ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ እንደገለጹት ኮሌጁ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለድኅረ ምረቃ ትምህርት መርሃ ግብሮች መስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን በ2014 ዓ/ም ብቻ 7 የ2ኛ ዲግሪና 1 የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ከፍቶ ሥራ መጀመሩን እንደ ማሳያ ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ታምሩ ገለጻ በ2015 ዓ/ም የጤና ኢንፎርማቲክስን ጨምሮ በሕክምና ት/ቤት በማሕጸን ሕክምናና በአጠቃላይ ቀዶ ጥገና የስፔሻሊቲ ፕሮግራሞችን እንዲሁም በሕክምና ቤተ ሙከራ ተጨማሪ 2 ፕሮግራሞችን ለመክፈት እየተሠራ ነው፡፡ የጤና ኢንፎርማቲክስ የትምህርት መስክ አዲስና እንደ ሀገር ከፍተኛ የሰው ኃይል እጥረት ያለበት ዘርፍ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ታምሩ በዚህ መስክ በመጀመሪያ ዲግሪ በሁለት ዙር ተማሪዎችን በማስመረቅ እንደ ኮሌጅ የ2ኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ለመጀመር የሚያስችል በቂ የሰው ኃይል፣ ልምድና ቤተ ሙከራዎችን ማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል፡፡

በኮሌጁ የጤና ኢንፎርማቲክስ ት/ክፍል ኃላፊ ረ/ፕ በእምነት ተካበ የጤና ኢንፎርማቲክስ የትምህርት መስክ የጤናውን ዘርፍ የሚመለከቱ የተለያዩ መረጃዎችን የማግኘት፣ የመተንተንና የማደራጀት ሂደትን ከኋላ ቀር አሠራሮች ለማላቀቅ ቴክኖሎጂንና የተለያዩ መተግበሪያዎችን መጠቀም የሚያስችልና ከተለያዩ የቴክኖሎጂ መስኮች ጋር ግንኙነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሀገራችን የጤና ሴክተር የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ትኩረት ከተሰጣቸው 4 ምሰሶዎች መካከል ዋነኛው የመረጃ አብዮትና የዲጂታላይዜሽን ጉዳይ ቢሆንም እንደ ሀገር በዘርፉ እየሠሩ ያሉ ሙያተኞች ቁጥር 10,344 ብቻ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው በዚህ ዙሪያ በተለያዩ የጤና ተቋማት በተደረገ የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ተቋማቱ የመስኩ ምሩቃንን ለመቅጠር ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

ከሥርዓተ ትምህርቱ ገምጋሚዎች መካከል ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጡት የመስኩ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ሙሉሰው አንዷለም በሰጡት አስተያየት ሥርዓተ ትምህርቱ ጊዜውን የዋጀ፣ የገበያ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንዲሁም የትምህርት ሚኒስቴር የሥርዓተ ትምህርት አዘገጃጀት መመሪያን መሠረት አድርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ የመርሃ ግብሩ መከፈት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን በመስኩ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ካላቸው ጥቂት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ እንደሚያደርገው የገለጹት ዶ/ር ሙሉሰው ሥርዓተ ትምህርቱን ለማሻሻል ሊስተካከሉ ይገባል ያሏቸውን አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡

በሥርዓተ ትምህርት ግምገማው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ተወካይን ጨምሮ፣ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጁ የሥራ ኃላፊዎችና መምህራን እንዲሁም የውጭ ገምጋሚዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት