የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ለሁሉም ካምፓሶች ለተመራቂ ተማሪዎች ወደ ሥራ ዓለም ሲገቡ ሊገጥሟቸው የሚችሉ የብልሹ አሠራር ችግሮችን የመከላከል ግንዛቤን ለማዳበር ከመስከረም 5-6/2015 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡  ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ እታፈራሁ መኮንን እንደገለጹት ተመራቂ ተማሪዎች በሙያቸው ለማገልገል ወደ ሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲሄዱ ያገኙትን ዕውቀት በመልካም ሥነ ምግባር ሥራ ላይ እንዲያውሉ ግንዛቤ ለማስጨበጥና እንደ ባለድርሻ አካል ኃላፊነት እንዲሰማቸው ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች የሀገር ተስፋ እንደ መሆናቸው በተማሩበት ሙያ በመልካም ምግባር፣ በአገልጋይነት መንፈስ፣ የሀገርን ጥቅም በማስቀደምና ፍትሐዊነትን መሠረት በማድረግ አገልግሎት እንዲሰጡም አሳስበዋል፡፡ 

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ ሥልጠናው ተመራቂ ተማሪዎች በዕውቀት፣ በክሂሎት፣ በሥነ ምግባር ታንጸው ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ በሕይወት የሚገጥማቸውን ፈተና የሚወጡበትን መንገድ ጠቋሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስኬታማ ሕይወት ለመኖር በትምህርት ጥሩ ውጤት ከማስመዝገብ በላይ በመልካም ሥነ ምግባር ታንጾ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ሙሉነህ የሀገር እድገት፣ ሰላምና ማኅበራዊ ግንኙነቶች በብልሹ አሠራርና በሙስና የሚጠቁ በመሆኑ ተመራቂዎች የሥነ ምግባር መርሆዎችን በማወቅና በመተግበር ለራስ፣ ለቤተሰብ እንዲሁም ለሀገር መልካም አርአያ መሆን ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ቤት መምህርና አሠልጣኝ ጋድሴንድ ኮኖፋ እንደገለጹት ሥልጠናው ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ያገኙትን ዕውቀት ሥራ ላይ ሲያውሉ በተለይም ከሥነ ምግባር ጋር ተያይዞ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ችግር ተረድተው በራሳቸው መፍታት እንዲችሉ ግንዛቤ የሚፈጥር ነው፡፡ የሥነ ምግባር ምንነትና አስፈላጊነት፣ 12ቱ መሠረታዊ የሥነ ምግባር መርሆዎች፣ የሥነ ምግባር ምንጮች፣ የመልካም ሥነ ምግባር አስፈላጊነት እና የሙስና ወንጀል በሥልጠናው ከተዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል መሆናቸውን አሠልጣኙ ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት