በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ በማኔጅመንት ትምህርት ክፍል በማርኬቲንግ ማኔጅመንት የ3 ዲግሪ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩት ዕጩ ዶ/ር ስንታየሁ አሰፋ ‹‹DRIVERS AND IMPEDIMENTS OF EXPORT PERFORMANCE፡ EVIDENCE FROM TEXTILE AND GARMENT ENTERPRISES IN ETHIOPIA››  በሚል ርዕስ የሠሩትን የምርምር ሥራ ኅዳር 7/2015 ዓ/ም የውጭና የውስጥ ገምጋሚዎች በተገኙበት አቅርበው ተገምግሟል፡፡  የመመረቂያ ጽሑፉም አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላቱ በአማካሪ ቦርዱ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ዕጩ ዶ/ር ስንታየሁ አሰፋ የመጀመሪያ ዲግሪውን በቢዝነስ ማኔጅመንት ከጂማ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የ2 ዲግሪውን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ያገኘ ሲሆን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ትምህርት ክፍል በመምህርነት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡  

በኢትዮጵያ መካከለኛና ከፍተኛ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት አምራቾች  ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለመላክ የሚያነሳሷቸው ምክንያቶችና በሂደቱ ውስጥ የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ላይ በማተኮር ጥናቱን እንዳከናወነ ዕጩ ዶ/ር ስንታየሁ ተናግሯል፡፡ እንደ ተመራማሪው ገለፃ ለገበያ የሚቀርበው ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት የተወዳዳሪነት ደረጃ ዝቅተኛ መሆን፣ የሰው ሀብትና የገንዘብ ዕጥረት እና መንግሥት ለዘርፉ የሚያደርገው ድጎማ ዝቅተኛ መሆን የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት በመስኩ የተሠማሩ ተቋማት ላይ ትኩረት አድርጎ ቢሠራ የተቋማቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ የመወዳደር ብቃትን ከፍ ማድረግ ይቻላልም ብለዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ ዕጩ ዶ/ር ስንታየሁ አሰፈ በኮሌጁ ታሪክ የመጀመሪያው የ3 ዲግሪ ምሩቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በምሩቁ የቀረበው የጥናት ጽሑፍም በውጭ ንግድ ላይ ያተኮረ በመሆኑ መንግሥት ለዘርፉ ከሰጠው ትኩረት አንፃር ሲታይ ጥናቱ ለዘርፉ ዕድገት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ እንደ ኮሌጁ ዲን በቀጣይም የ3 ዲግሪ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ተማሪዎች አስፈላጊውን የትምህርት ግብዓት በማሟላትና ድጋፍ በመስጠት ትምህርታቸውን በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ እንዲጨርሱ በትኩረት ይሠራል፡፡

የድኅረ ምረቃ ት/ቤት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አበራ ኡንቻ በበኩላቸው ምሩቁ ትምህርቱን በተቀመጠለት የ4 ዓመት ጊዜ ውስጥ የጨረሰ መሆኑ ለሌሎች ተማሪዎች ጥሩ ተሞክሮ እንደሚሆን ገልፀው ት/ቤቱ ሁሉም የድኅረ-ምረቃ ተማሪዎች በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ አዳዲስ የድጋፍና ክትትል አሠራሮችን ዘርግቶ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዕለቱ በውጭ ገምጋሚነት የተገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ ማቴዎስ አንሰርሙ የዕጩ ዶ/ር ስንታየሁ መመረቂያ ጽሑፍ ከመገምገሚያ መስፈርቶች አንጻር በጥሩ ሁኔታ የቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መሰል የምርምር ሥራዎች በቀጣይ ጊዜያት የማኅበረሰቡን ብሎም በዘርፉ ያሉትን ሀገራዊ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ በመሆናቸው ተመራማሪው የጥናት ውጤታቸውን በተለያዩ የምርምር መጽሔቶች ላይ እንዲታተሙ በማድረግ ለተደራሽነቱ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

ዕጩ ዶ/ር ስንታየሁ የዶክትሬት ዲግሪው በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ከጸደቀ በኋላ የሚያገኝ ሲሆን በመርሃ-ግብሩ ላይ የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ፣ የዘርፉ መምህራንና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡              

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት