ዓለም አቀፍ የነጭ ሪባን ቀን “ሴቷን አከብራለሁ! ጥቃቷንም እከላከላለሁ!”  በሚል መሪ ቃል ከሳውላን ካምፓስ ውጪ ባሉ በዩኒቨርሲቲው 5 ካምፓሶች ኅዳር 19/2015 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡ በዓሉም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ31 ጊዜ በሀገራችን ለ17 ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የነጭ ሪባን ቀን ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ሲከበር ወንዶች ነጭ ሪባን በማድረግ የፆታን ጥቃት እንደሚቃወሙ እና በሴቶችና ወንዶች እኩልነት እንደሚያምኑ አቋማቸውን የሚገልጹበት ነው፡፡ በዓሉ ወንዶች የሴት እህቶቻቸውን ጥቃት በመከላከል ሂደት ውስጥ አጋርነታቸውን የሚያሳዩበትና በሴቶች ላይ ጥቃት ላለማድረስ እንዲሁም ጥቃት ሲደርስባቸው ዳር ቆሞ ላለመመልከት ቃል የሚገቡበት መሆኑን  ፕሬዝደንቱ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ዳምጠው አክለውም ሁላችንም ወንዶች በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በዩኒቨርሲቲው ውጪ የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶችን በቁርጠኝነት ለመዋጋት ቃል እየገባን ሴቶችን በሁሉም የልማት ዘርፎች እኩል በማሳተፍ ለሀገራችን ኅዳሴ የበኩላችንን እንወጣ ብለዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለሀገራችን ዕድገት የተሻለ አስተዋጽኦ ለማበርከት የዩኒቨርሲቲው አመራር አካላትና መ/ራን በሴት ተማሪዎች ዙሪያ የሚጠበቅብን ዋነኛውና የመጀመሪያው ድርሻችን ለትምህርት ተመድበው ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡ ሴት ተማሪዎችን ውጤታማ የሚያደርጉ ሥራዎችን በትኩረት መሥራት እንደሆነ ፕሬዝደንቱ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉ/ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሰናይት ሳህሌ እንደገለጹት ፆታዊ ጥቃት በሴቶች ላይ የሚፈጸም አካላዊ፣ ሰብዓዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን የሚያስከትል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲሆን በግልም ሆነ በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ የሚያሳድር ብሎም በሀገራችን ሕጎች የተረጋገጡ መሠረታዊ ነፃነቶችና መብቶች ላይ ያለአግባብ ጣልቃ ገብነትን የሚያሳይና መብቶችን የሚገድብ ድርጊት ነው ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በ2008 ዓ/ም በተካሄደው የኢትዮጵያ ሕዝብና ጤና ጥናት ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በቤትና ከቤት ውጪ በስፋት የሚፈጸሙ እንደሆነ ያትትና የጥቃቱ ዋነኛ ሰለባዎች ሴቶችና ሕጻናት እንደሆኑ ያስቀምጣል ብለዋል፡፡ እንደ ተቋምም ከሚመጡ ጉዳዮች መካከል በሴት ተማሪዎች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶች መካከል ወሲባዊ ትንኮሳና ጥቃት ሰፊውን ድርሻ እንደሚይዝ ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል፡፡ ፆታዊ ጥቃትን ማስወገጃ ቀናቶችም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለማስቀረት የሚደረግ የትግል አካል በመሆኑ ወንዶች ሪባኑን አድርገው በሴቶች ላይ ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት ፈጽሞ ለላመፈጸምና ጥቃቱ በሌሎች ሲፈጸምም ዝም ብሎ ላለማየት ቃል የሚገቡበት መለያ ምልክት በመሆኑ ሁላችንም ይህንን ጥቃት እንደራሳችን ሕመም በመቁጠር ትኩረት ሰጥተን እንሥራበት ሲሉ ዳይሬክተሯ ጠይቀዋል፡፡   

ፆታዊ ትንኮሳና ያልተገባ ባህሪያት ከሕግ አንጻር እንዴት እንደሚታዩና የሴቶች ሰብዓዊ መብቶች በዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ሕጎች ዕይታ ምን እንደሚመስል በዝርዝር ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት መ/ር አብርሃም ክንፈ እንደገለጹት ሴቶች በዘመናት በተለያየ መንገድ አድሏዊ ተግባራት ሲፈጸሙባቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ብዙ ጥቃቶች እንደሚደርሱባቸውና ጥቃትና መድሎዎቹም ባደጉትም ሆነ በማደግ ላይ ባሉት ሀገራት የሚስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ችግሩ ዓለም አቀፋዊ እንደመሆኑ መጠን በተለይ ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ የሥርዓተ ፆታ ጉዳይ ትኩረት አድርጎ ብዙ የዓለም ዓቀፍ፣ አህጉር አቀፍና ሀገር አቀፍ ስምምነቶችና ሕጎች ተደንግገው እንደሚገኙና በባህርይ ደረጃም እነዚህ መብቶች የማይገሰሱ፣ የማይገፈፋ፣ ዓለም ዓቀፍ የሆኑና የማይነጣጠሉ መሆናቸውን መ/ር አብርሃም አብራርተዋል፡፡

ሰብዓዊ መብቶች ከዓለም ዓቀፍ እና አህጉራዊ ሕግጋት አንጻር የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር የሴቶችን የእኩልነት መብት መሠረታዊ መብት በማድረግ ያካተተ ሠነድ ሲሆን የሴቶች የእኩልነት መብት ሳይከበር የሴቶችን መብት እና የዓለምን ሠላም ማስጠበቅ የማይቻል መሆኑን እንደሚያመላክት መ/ር አብረሃም ገልጸው በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መገለጫ  ሰዎች ሁሉ የማይገረሰስ እኩል መብት እና ክብር ያላቸው ስለመሆኑና ይህም ለዓለም ሠላም መከበር እና ለሰው ልጆች መሠረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች መረጋገጥ ሚና እንዳለው መደንገጉን ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በዩኒቨርሲቲው ፀረ-ፆታዊ ትንኮሳንና ያልተገባ ባሕርይን ለማስወገድ የወጣውን ደንብ አስመልክቶ  በዩኒቨርሲቲው ያለ ማንኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ያለምንም ገደብ መውጣትና መግባት፣ መማር ማስተማር የሚችልበት፣ ጫናና መሸማቀቅ ሳይኖር የግለሰቡ ደኅንነት ተጠብቆ ምንም ዓይነት ፆታዊ ትንኮሳና ያልተገባ ድርጊት ሳይፈጸምበት ምቹ አካባቢ ተፈጥሮለት በሠላም የዕለት ተዕለት ሥራውን እንዲሠራ ለማስቻል ያለመ መሆኑን መ/ር አብረሃም ገልጸዋል፡፡ ደንቡም በዩኒቨርሲቲው የስርዓተ ፆታ ጉዳዮች ቢሮ አማካኝነት ተዘጋጅቶ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት አጽድቆት ከጥቅምት 12/ 2002 ዓ/ም ጀምሮ እያገለገለ ያለ ገዢ ሕግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሴቶችን ጥቃትና ትንኮሳ ለመከላከል ዳይሬክቶሬቱ የሚሠራቸውን ዋና ዋና ሥራዎች በዝርዝር ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ዛፉ ዘውዴ  በበኩላቸው ዳይሬክቶሬቱ የነጭ ሪባን ቀንን ጨምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመጡ ሴት ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም የማዘጋጀት፣ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የሕይወት ክሂሎት፣ በስነ-ተዋልዶ ጤና፣ ፆታን መሠረት ያደረጉ ትንኮሳዎች፣ ሥርዓተ ፆታ፣ ፆታዊ ትንኮሳና ጥቃትን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ለተማሪዎችና ሠራተኞች ጥቃትን የመከላከል እንዲሁም ጥቃት ደርሶባቸው አቤቱታ ይዘው ለሚመጡ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ዳይሬክቶሬቱ የበኩሉን ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንዳለ አቶ ዛፉ አክለዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የተለያዩ አስተማሪ የሆኑ መነባንቦችና ግጥሞች የቀረቡ ሲሆን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት ያደረጉ አስተያየቶችና ጥያቄዎችም ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት