በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ9ኛ ጊዜ በተከበረው የኢንተርፕሪነርሺፕ ሳምንት ላይ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ወክላ የቀረበችው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል 4ኛ ዓመት ተማሪ ሱመያ ፌቲ ባቀረበችው የቢዝነስ ሃሳብ 2ኛ በመውጣት ኅዳር 25/2015 ዓ/ም ከሥራና ክሂሎት ሚኒስቴር 260 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆናለች፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ የኢንተርፕሪነርሺፕ ሳምንት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከበር ተማሪ ሱመያ ባቀረበችው የቢዝነስ ሃሰብ 1ኛ መውጣቷን አስታውሰው በሀገር አቀፍ ውድድሩ ከመላው ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክና ሙያ ት/ቤቶች ከተወጣጡ ተወዳዳሪዎች መካከል በ2ኛነት መሸለሟን ተናግረዋል፡፡ ሽልማቱ ተማሪዎች የሥራ ፈጠራ ዕይታቸውን እንዲያሰፉ የሚያበረታታ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ወንድወሰን ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን በአካባቢያቸው ባለው መልካም አጋጣሚ ትኩረት አድርገው መሥራት ከቻሉ ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች የሚተርፉ ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሆኑና ኢኮኖሚያቸውን እንዲያሳድጉ ያስችላቸዋልም ብለዋል፡፡

የማዕከሉ አስተባባሪ አቶ አበበ ዘየደ በበኩላቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባስተላለፈው ጥሪ መሠረት ተማሪዋን ለውድድር ማቅረባቸውን ገልጸው ለማሸነፍ የሚረዳት አስፈላጊ ሙያዊ ድጋፍ እንደተደረገላት ተናግረዋል፡፡ በውድድር ሂደቱ የተሻሉ ሃሳቦችን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚረዷቸው የተለያዩ ባንኮች ተወካዮች፣ ኢኖቬሽን ሚኒስቴርና የቀጠናዎች ትስሰር ሚኒስቴር በባለድርሻነት ቀርበው የጋራ ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ አስተባባሪው የተማሪዋ የፈጠራ ሃሳብ እውን እንዲሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

‹‹ሙዜ ቃጫ›› በሚል ርዕስ ከሙዝ ግንድ ቃጫ የማምረት ሥራ ላይ የቢዝነስ ሃሳብ ይዛ የቀረበችው ተሸላሚ ተማሪ ሱመያ ፌቲ አርባ ምንጭና አካባቢዋ የሙዝ ምርት በስፋት የሚመረትበት መሆኑን እንደመልካም አጋጣሚ ጠቅሳ ከሙዝ የሚገኘውን ተረፈ ምርት የአካባቢው ማኅበረሰብና አምራቹ በተገቢው መልኩ እየተጠቀመ አለመሆኑ ለፈጠራ ሃሳቡ አነሳስቶኛል ብላለች፡፡ ከሚመረተው ቃጫ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ ምርቶችን ማዘጋጀት እንደሚቻልም ተናግራለች፡፡ እንደ ተማሪ ሱመያ የሚጣለውን የሙዝ ግንድ ወደ ተሻለ ምርት መቀየር ከተቻለ አካባቢን ከቆሻሻና ብክለት ከመከላከል ባሻገር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመቀነስ ይረዳል፡፡ በተጨማሪም ከቃጫ የሚመረተው የንጽህና መጠበቂያ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከአፈር ጋር መዋሃድ የሚችል በመሆኑ የአፈር መበከልን የሚያስቀር ነው፡፡

ተማሪ ሱመያ በሀገራችን የሚስተዋለውን የሥራ አጥ ቁጥር ማደግና የፍልሰት መስፋፋት ለመቅረፍ ሥራን ከመንግሥት ከመጠበቅ ይልቅ በአካባቢያችን የሚገኙ መልካም አጋጣሚዎችን ተጠቅመን ሥራ ፈጣሪ መሆን ይጠበቅብናል ብላለች፡፡ ባገኘችው ሽልማት መደሰቷንና ሃሳቧን ወደ ተግባር ለመለወጥ መነሳሳትን እንደፈጠረላትም ተናግራለች፡፡

                                                                                                                                         የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት