የጋሞ ዞን አስተዳደር አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በጋንታ ኦቾሌ ቀበሌ የሚገኘውን ሦስት ሄክታር የጫሞ ሐይቅ ረግረጋማ መሬት መልሶ እንዲለማ ለሌቶ ዓሣ አስጋሪዎች ማኅበር ጥር 22/2015 ዓ.ም በይፋ አስረክቧል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጨኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ  ም/አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ገዙ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከአራት ዓመት በፊት ባካሄደው ጥናት የጫሞ ሐይቅ አደጋ ላይ መሆኑንና በደለል እየተሞላ መሆኑን በመጥቀስ በሐይቁ ዙሪያ ያለውን ረግረጋማ መሬት ከሌቶ ዓሣ አስጋሪዎች ማኅበር ጋር በጋራ በማልማት ሐይቁን ለመታደግ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ“AMU-IUC” ፕሮግራም አማካኝነት ባቀረበው ጥያቄ  መሠረት በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በጋንታ ኦቾሌ ቀበሌ ከአርትሚዚያ ኢንቨስትመንት እርሻ ቀጥሎ የሚገኘውን ሦስት ሄክታር የሐይቁን ረግረጋማ መሬት ለማኅበሩ በይፋ ማስረከብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ አቶ ሚሊዩን አክለው እንደተናገሩት ቦታውን የተረከበው ማኅበር ወደ አካባቢው ለሚመጡ እንግዶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ምቹና ከተፈጥሮው ጋር የሚስማማ የመዝናኛ ቦታ ከመገንባት ባሻገር ሐይቁን የሚታደጉ ሥራዎችን  መሥራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ“AMU-IUC” ፕሮግራም ማኔጀር ዶ/ር ፋሲል እሸቱ በበኩላቸው እ.እ.አ በ2018 ዓ.ም ጥናቱ ከተጠናቀቀ ጊዜ ጀምሮ የቦታ ጥያቄው ለዞኑና ለወረዳው ሲቀርብ መቆየቱን አስታውሰው ጥያቄው ምላሽ አግኝቶ የዞኑና የወረዳው አመራሮች በተገኙበት የመሬት ርክብክብ በመደረጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ፋሲል የሐይቁን ዙሪያ ወደነበረበት መመለስ፣ ወደ ሐይቁ የሚገባውን ደለል ለመከላከልና በሐይቁ ውስጥ እየቀነሰ የመጣውን የዓሳ ሀብት ወደ ቀድሞ ለመመለስ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ፋሲል ሐይቁን ለመታደግ ዩኒቨርሲቲው በሐይቁ ዙሪያ ከ70 ዓመታት በፊት የጠፉ ተክሎችን መልሶ በመትከልና በመንከባከብ ወደ ሐይቁ የሚገባውን ደለል ለመቀነስ የሚያስችል የትብብር ፕሮጀክት ከ“AMU-IUC” ፕሮግራም፣  ከሮማንና ኃይለማርያም ፋውንዴሽን እና ከቤልጂየሙ ኬዩሊቨን ዩኒቨርሲቲ/KU Leuven University/ ጋር ተቀርፆ አየተሠራ ነው፡፡ ማኅበሩ በተረከበው ቦታ ላይም ይኸው ሐይቁን የመታደግና መልሶ የማልማት ሥራ የሚሠራ ሲሆን ከዚህም ባሻገር በቦታው ላይ ወደ አካባቢው ለሚመጡ እንግዶች የሚሆን ከተፈጥሮው ጋር የሚስማማ የመዝናኛ ስፍራ ለመገንባት መታቀዱንም ዶ/ር ፋሲል ጠቁመዋል፡፡

የሌቶ ዓሳ አስጋሪዎች ማኅበር ሒሳብ ሹም አቶ ተሾመ ታደለ መሬቱ ለማኅበራቸው በመሰጠቱ በጣም  እንደተደሰቱ ገልጸው በራሳቸውና በሌቶ ዓሣ አስጋሪዎች ማኅበር ስም ለዞኑና ለወረዳው አመራሮች በተለይም ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ማኅበራቸው በቦታው የተለያዩ የረግረጋማ ቦታ ተክሎችን  በመትከልና በመንከባከብ ከማልማት ባሻገር ቦታውን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ስብሰባዎች፣ ሠርጎችና ልዩ ልዩ ተግባራት የሚከናወኑበት የመዝናኛ ስፍራ የማድረግ ራዕይ መሰነቁን አቶ ተሸመ ገልጸዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የጋሞ ዞንና የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት