የትምህርት ጥራትንና የተማሪዎችን ውጤት በዘላቂነት ለማሻሻል የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻዎች በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ት/ቤት ኃላፊዎችና በ2014 ዓ/ም በ12 ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የ2014 ዓ/ም የ12ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና የአፈታተን ሥርዓቱ ያልተለመደና ስርቆትን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የተቻለበት በመሆኑ እንደሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣው የተማሪዎች ውጤት የትምህርት ሥርዓቱ ምን እንደሚመስል ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል ብለዋል፡፡ ከ8 መቶ ሺህ በላይ ተፈታኝ ተማሪዎች 3.3% ብቻ ተማሪ ማለፊያ ነጥብ ማምጣቱ እንደሀገርም ሆነ እንደከፍተኛ ተቋም የሚሠሩ ብዙ ሥራዎች እንደሚጠብቁን ያመላከተ ፈተና መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

በማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ከሚመሩ ዘርፎች የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት አንዱ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ከማቆያ እስከ 12 ክፍል የያዘው የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት የ2014 ዓ/ም የ12 ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ውጤት ትንተና እንደሚያሳየው ከፍ ያሉ ውጤቶች ቢኖሩም ቁጥራቸው ግን በጣም ጥቂት መሆኑን ገዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ተክሉ በግል ደረጃ ሲታይ ከ600 በላይ አንድ ተማሪ እና ከ500-600 ወደ 5 የሚሆኑ ተማሪዎች ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን በጥቅሉ ከ50% በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች 22.7% ብቻ ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው 2 ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ካሣሁን ድጤ እንደገለጹት የ12 ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል በተፈጥሮ ሳይንስ የተመዘገቡ ተማሪዎች 81 ሲሆኑ በማኅበራዊ ሳይንስ 55 ባጠቃላይ 136 ተማሪዎች ፈተናውን መውሰዳቸውን አስታውሰዋል፡፡ ከ50% በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች 31 ብቻ ሲሆኑ በትምህርት ቤቱ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት በተማሪ ቢኒያም ጩንጬ የተመዘገበው 629 ነጥብ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ካሣሁን ከተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት በመነሳት ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር በመቀራረብና በመመካከር የትምህርት ጥራትንና የተማሪዎችን ውጤት በዘላቂነት ለማሻሻል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በትኩረት መሥራት በሚገባን ወሳኝ ሰዓት እንገኛለን፡፡

የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤቶች ሥራ አስኪያጅ አቶ ስላስ ጎዳና በበኩላቸው የ2014 ዓ/ም የ12 ክፍል መልቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ስርቆትን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በመቆጣጠር ተፈታኞች በራስ ጥረት ብቻ እንዲሠሩ ሆኖ የተጠናቀቀ ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ የትምህርት ሥርዓታችን ጥራት ላይ ትኩረት ሳያደርግ በመቆየቱና ተማሪዎች ኩረጃን ባህል እስከማድረግ ደርሰው እንደአቋራጭ መፍትሄ በመጠቀም እራስን በዕውቀት የመገንባት ጥረታቸው እጅግ በመዳከሙና በሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች የተመዘገበው ውጤት እንደሀገር እጅግ ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ የሚፈተኑ የት/ቤታቸው ተማሪዎች እጅግ ፈታኝ በሆነው ዓመት ተፈትነው ለዞኑም ሆነ ለክልሉ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ የት/ቤቱን ተማሪዎች እንደ መልካም አርአያ በመከተል እንዲበረታቱ አሳስበዋል፡፡

በብሔራዊ ፈተናው ውጤት 629 ነጥብ ያመጣው ተማሪ ቢኒያም ጩንጬ በሰጠው አስተያየት ከ1-12 ክፍል ትምህርቱን የተከታተለው በኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ሲሆን በመምህሮቼና ወላጆቼ ድጋፍ፣ የራሴም ጥረት ታክሎበት ጊዜን በአግባቡ በመመደብና የራሴን የአጠናን ዘዴ በመከተል፣ የመርጃ መጽሕፍትን በአግባቡ በመጠቀም፣ መምህራንን በልዩ ትኩረት በመከታተልና ያልገቡኝን ጉዳዮች ማብራሪያና ምሳሌዎችን በመጠየቅ በአግባቡ በመረዳት፣ አዳዲስ የሆኑ ሃሳቦችን በልዩነት በማስታወሻ መዝግቤ በመያዝና ሌሎችንም ለትምህርቴ አጋዥ የሆኑ ተግባራትን በመፈጸም ትምህርቴን በመከታተሌ ውጤታማ ለመሆን በቅቻለሁኝ ብሏል፡፡ ተማሪ ቢኒያም በቀጣይ ለሚፈተኑ ተማሪዎች ለትምህርታቸው ብቻ አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች ውጪ ቴክኖሎጂ በበዛበት በዚህ ዘመን በስልክ፣ በቴሌቪዥን፣ በፌስቡክና ሌሎች ማኅበራዊና ብሮድካስት ሚዲያዎች ላይ ውድ ጊዜያቸውን በማበከን መሸወድ እንደሌለባቸው ምክሩን ለግሷል፡፡

በብሔራዊ ፈተናው 502 ነጠብ ያመጣቸው እንስት ተማሪ ቤቴልሄም መንገሻ በበኩሏ ከፍተኛ ውጤት በማምጣቷ ደስተኛ መሆኗን ገልፃ ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ራስን በሚገባ ማዘጋጀት ተገቢ ነው ብላለች፡፡ እንደቤቴልሄም የትምህርት ሥርዓቱና የአፈታተን ሂደቱ እየተቀየረ ስለሆነ ወላጆች ልጆቻቸውን የዕለቱን ትምህርት በየለቱ እንዲያነቡ ክትትል ማድረግ እንደሚገባና እንደቤተሰብም ማንኛውም ቤተሰብ ለልጁ ሊያወርሰው የሚገባው ውድ ነገር ትምህርት ብቻ መሆኑን ተናግራለች፡፡ ተማሪዎችም በበኩላቸው በመልካም ሥነምግባር ቢታነጹና ጥሩ የሆነ ነገር ምርጫቸው ቢያደርጉ በተለይ ሴት ተማሪዎች ስኬታማ ለመሆን ያሉባቸውን ኃላፊነቶችን በጥንቃቄ በመወጣትና ለትምህርት በቂ ጊዜ በመስጠት መማር እንደሚገባቸው እንጂ ፈጽሞ ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባቸው መክራለች፡፡

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት