የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማኅ/ጉድ/ማስ/ጽ/ቤት ለ3 አቅመ ደካማ እናቶች ነፃ የማሕፀን ውልቃት ቀዶ ጥገና ሕክምና አገልግሎት በገረሴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በኮሌጁ የማሕፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪሞችና መምህራን መጋቢት 7/2015 ዓ/ም እንዲሰጥ አድርጓል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የማኅ/ጉድ/ማስ/ጽ/ቤት ኃላፊ ረ/ፕ ገሊላ ቢረሳው ኮሌጁ በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ በኮሌጁ የሚገኙ የጤናና ሕክምና ባለሙያዎችን በመጠቀም በተለያዩ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ሙያዊ ድጋፎችን እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ በድል ፋና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ በቆላ ሼሌና በብርብር ጤና ጣቢያዎች አንድ ጠቅላላ ሐኪም፣ ነርስ፣ የሚድ ዋይፍሪና የላቦራቶሪ ባለሙያዎችን ያካተተ የሕክምና ቡድን በሳምንት ሁለቴ እየተላከ በቋሚነት ነፃ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በተጨማሪም በአርባ ምንጭ ከተማ ድል ፋና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የውስጥ ደዌና የሕፃናት ሕክምና ስፔሻሊስቶች በቋሚነት ነፃ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በኮሌጁ የሚገኙ የክሊኒካል ሚድ ዋይፍሪ ባለሙያዎች በጨንቻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለ15 ቀን በመቀመጥ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንም አውስተዋል፡፡

በገረሴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በቋሚነት የሚሰጠው የማሕፀን ውልቃት ቀዶ ጥገና ሕክምና አገልግሎት ከዚህ አንፃር ተጠቃሽ አገልግሎት መሆኑን የገለጹት አስተባባሪዋ በቅርቡ የሆስፒታሉን ፍላጎት መሠረት በማድረግ የውስጥ ደዌና የሕፃናት ስፔሻሊቲ ሕክምና ይጀመራል ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ስፔሻሊቲ ሐኪሞች የሚሳተፉበት ቋሚ አገልግሎት በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ጭምር የሚሰጥ ሲሆን በቀጣይ ኮሌጁ ሙያዊ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ዘርፎችንና የጤና ተቋማት የማስፋት ዕቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑንም ረ/ፕ ገሊላ አክለው ተናግረዋል፡፡

የገረሴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ማንደፍሮት ሽብሩ ሆስፒታሉ በዋናነት በገረሴ ከተማ፣ በገረሴ ዙሪያ፣ በቦንኬና በአጎራባች ወረዳዎች የሚገኙ ከ226 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እያገለገለ ይገኛል ብለዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ጊዜያት ለሆስፒታሉ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን የተናገሩት አቶ ማንደፍሮት በተለይ በማሕፀን ውልቃት ቀዶ ጥገና ሕክምና ላይ በቋሚነት እየተሰጠ ያለው አገልግሎት በርካታ አቅመ ደካማ እናቶችን ከስቃይ ከመታደጉ ባሻገር ሕክምናውን ለማግኘት ሲባል ወደ ሌሎች ከተሞች በመሄድ የሚወጣን ገንዘብ፣ የጊዜ ብክነትና እንግልት ያስቀረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የእናቶችና ሕፃናት ሕክምና ሆስፒታሉ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው መስኮች  ዋነኞቹ መሆናቸውን ያወሱት ሥራ አስኪያጁ ዩኒቨርሲቲው በመስኩ እየሰጠ ያለው ድጋፍ ከዚህ አንፃር ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡  እንደ ሥራ አስኪያጁ ዩኒቨርሲቲው በሆስፒታሉ ለሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች ነፃ የትምህርት ዕድል በመስጠት እያስተማረ መሆኑ የሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጥና የደንበኞች እርካታ ከፍ እንዲል ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና የማሕፀንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ተሾመ ወልደሃና ማሕፀን በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጥሮ ቦታውን ለቆ ወደታች በመንሸራተት በብልት ጫፍ ላይ ሲመጣ ወይም ሙሉ በሙሉ ከብልት ሲወጣ የማሕፀን ውልቃት/መንሸራተት እንደሚከሰት ገልጸዋል፡፡ በገጠር የሚኖሩ እናቶች በአብዛኛው ለዚህ ችግር ተጋላጭ መሆናቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ተሾመ በርካታ ልጆችን አምጦ መውለድ፣ ከባድ ዕቃ መሸከም፣ ረጅም መንገድ በእግር መጓዝና ሌሎች መሰል ሁኔታዎች ለዚሁ ችግር የሚዳርጉ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡ የማሕጸን ውልቃት ችግር የገጠማቸው እናቶች ሰገራና ሽንት አለመቆጣጠር፣ የብልት መቁሰል፣ የሽንት ኢንፌክሽንና ለመሳሰሉ የጤና እክሎች ስለሚዳረጉ ለከፍተኛ ሥነ-ልቦናዊ ችግር እንደሚጋለጡ ያወሱት ዶ/ር ተሾመ በቀጣይ ጊዜያትም እናቶች ከመሰል ችግርና የሥነ-ልቦና ጫና እንዲላቀቁ ተመሳሳይ የሕክምና አገልግሎት በሌሎችም የጤና ተቋማት ተገኝተው ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ኮሌጁ በ2015 በጀት ዓመት አገልግሎቱን ሲሰጥ ለ2 ዙር ሲሆን እስካሁን ችግሩ ለተከሰተባቸው 11 እናቶች አገልግሎቱ ተሰጥቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት