የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሥነ- ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት በ2015 የትምህርት ዘመን አዲስ ለገቡ ተማሪዎች በዋናው ግቢ እና ጫሞ ካምፓስ በሥነ-ምግባር ምንነት፣ መሠረታዊ መርሆዎች፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ሥነ-ምግባር መመሪያና በሙስና ወንጀል ዙሪያ መጋቢት 23/2015 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶ ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ እንደገለፁት በሥነ-ምግባር ያልተገነባ ትውልድ ለሀገርም ሆነ ለቤተሰብ አስቸጋሪ ስለሚሆን ወጣቱን ትውልድ በተለይ ተማሪዎችን በሥነ-ምግባር ማነጽና መገንባት ከሙስና የፀዳ ተቋምና ሀገር ለመፍጠር ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ እታፈራሁ መኮንን ሥልጠናው ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን ሥነ-ምግባራዊ ባህሪያትና እሴቶች በመላበስ ሙስናና ብልሹ አሠራርን የሚፀየፉ እንዲሆኑ ማስቻልና በዕውቀት፣ በክሂሎትና አስተሳሰብ የተሻሉ እንዲሆኑ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ወ/ሮ እታፈራሁ አክለውም እንደተናገሩት ሥልጠናው ተማሪዎቹ ለተቋሙ አዲስ እንደ መሆናቸው የመጡበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ሊከተሏቸው የሚገቡ ባህሪያት እና ሊኖሯቸው የሚገቡ ሥነ-ምግባሮች እንዲሁም በተማሪዎች የሥነ-ምግባር መመሪያና በሙስና ወንጀል ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡

የሕግ ትምህርት ቤት መምህርና አሠልጣኝ አቶ ጎድሴንድ ኮኖፋ በበኩላቸው ሥልጠናው ተማሪዎች በሥነ-ምግባርና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ዲስፕሊን መመሪያ ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የታለመ ሲሆን ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በባህርይ እና በሥነ-ምግባር የታነፁ እንዲሁም በክሂሎትና ዕውቀት የበቁ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሠላማዊ እንዲሆን፣ ተማሪዎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው በመልካም ሥነ-ምግባር ታንፀው በመውጣት በሙያቸው ሀገርን እንዲያገለግሉ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አቶ ጎድሴንድ አክለዋል፡፡  

ሠልጣኝ ተማሪ አማኑኤል ጴጥሮስ በበኩሉ በሰጠው አስተያየት ሥልጠናው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሊከተሏቸው የሚገቧቸውን የሥነ-ምግባር መርሆዎች እንዲረዱና በቀጣይ የተጣለባቸውን ሀገራዊና ሕዝባዊ አደራ በብቃት፣ በታማኝነትና በቅንነት እንዲሁም በስኬት ለመፈፀም የሚያስችልና ሁሉም ተማሪዎች ተግባራዊ ማድረግ የሚገባቸው መሆኑን ግንዛቤ ማግኘቱን ገልጿል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት