አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከደ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግሥት መስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በጎፋ ዞን መሎኮዛ ወረዳ በጫልቆ ወንዝ ላይ የሚገነባውን የጫልቆ ግድብና መካከለኛ የመስኖ ጥናትና ዲዛይን ንድፍ ሪፖርት ግምገማ ከመጋቢት 26 - 27/2015 ዓ.ም አካሂዷል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደገለጹት ሀገራችን ኢትዮጵያ በርካታ የውኃ ሀብትና ሰፊ የእርሻ መሬት ያላት ቢሆንም በአግባቡ ተጠቅሞ ወደ ሥራ የሚቀይር በቂ የሠለጠነ  የሰው ኃይል ባለመኖሩ ሀገር ለድርቅ መጋለጧን አመላክተው ይህም በውሃ ዘርፍ ላይ ላሉ ባለሙያዎች የሚያስቆጭ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዓለማየሁ አክለውም በቀጣይ ከረሃብና ከተመጽዋችነት ለመላቀቅ ያለንን ጊዜ፣ ጉልበትና ዕውቀት በመጠቀም በመስኖ ማልማት አማራጭ የሌለው መሆኑን ጠቁመው የዩኒቨርሲቲው ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በርካታ ባለሙያዎችን ከማፍራት ባሻገር የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ዲዛይንና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ኃላፊ እና የቀድሞ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሱፐርቫይዘር ቦርድ አባል አቶ ውባየሁ ትዕዛዙ በበኩላቸው ከዩኒቨርሲቲው ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር ላለፉት አሥር ዓመታት የዲዛይንና የግንባታ ሥራዎች በጋር እየሠሩ መቆየታቸውንና ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸው በአሁኑ ወቅት ስምንት ሺህ ሄክታር ሊያለማ የሚችል የመስኖ ግድብና ተያያዥ ሥራዎች ጥናት እየሠሩ መሆናቸውን እንዲሁም በጎፋ ዞን መሎኮዛ ወረዳ የጫልቆ መለስተኛ የመስኖ ግድብና ተያያዥ ሥራዎችን ሠርተው ለግምገማ መቅረቡን ተናግረዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጉድኝት እና ከጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል ጋርም ሌሎች በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ እንዳሉ አቶ ውባየሁ ጠቅሰዋል፡፡  

በሀገራችን በውኃው ዘርፍ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አነስተኛ ናቸው ያሉት የደቡብ ክልል ውኃ መስኖ ኤጀንሲና ልማት ጥናትና ዲዛይን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ባህሩ ዓለሙ በመካካለኛ ግድብ ግንባታዎች ደረጃ ጅምር ግንባታዎች እንዳሉና በተለያዩ የግንባታ ሥራዎች ላይ ያተኮሩ ከ12 በላይ የሚሆኑ ጥናቶች የተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ባህሩ አክለውም ከምርምር ተቋማት ጋር በመሥራታቸው ጥናቶች በሚካሄዱበት ወቅት ያጋጥም የነበረው የአማካሪዎች እጥረት ተቀርፏል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲውና የደቡብ ዲዛይንና ግባታ ልማት ኤጀንሲ በጋራ የአዋጭነት ጥናት  መሥራታቸውን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው ውኃ ቴክኖሎጂ  ኢንስቲትዩት መ/ር እና ተማራማሪ እንዲሁም የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ዶ/ር ታምሩ ተሰማ ጥናቱ ሦስት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያውና የሁለተኛው ደረጃ የአዋጭነት ጥናት ተጠናቆ  ወደ ዋናው ሥራ ለመግባት ያመች ዘንድ የዲዛይን ንድፉን በባለድርሻ አካላት ለማስገምገም መድረኩ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  የጥናቱ አሠሪ ድርጅትም የደቡብ ክልል መስኖ ኤጀንሲ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጫልቆ መስኖ ግድብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ (Socio-economic) ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ጥናት ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና የኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መ/ር አቶ ስለሺ አበበ እንደገለጹት የጥናቱ ዲዛይን ሥራ ሲጠናቀቅ አርሶ አደሩ ዝናብን ሳይጠብቅ ክረምት ከበጋ ማምረት እንዲችል፣ በአካባቢው ከተለመዱት ምርቶች ውጪ አዳዲስ ምርቶችን በማምረት ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝና የአርሶ አደሩ የኑሮ ሁኔታ በዘላቂነት እንዲሻሻል እንዲሁም ለውጪ ገበያ የሚውሉ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሪ እንዲገኙና የዘይት መጭመቂያና ሌሎችም አግሮ ኢንዱስትሪዎች ወደ አካባቢው እንዲመጡ የሚረዳ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ይዞ እንደሚመጣ አመላክተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም በግምገማው ገንቢና ጠቃሚ ሃሳቦች እንደተነሱ ገልጸው የተነሱ ሃሳቦችንና ጠንካራ አስተያየቶችን በመውሰድ ለቀጣይ ሥራዎች እንደ ግብዓት እንደጠቀሙ ተናግረዋል፡፡

በግምገማ መድረኩ 18 ጥናታዊ ጹሑፎች ቀርበው ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን የዩኒቨርሲቲውን አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ጨምሮ የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር፣ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፣ መ/ራን እና ተመራማሪዎች፣ የደቡብ ዲዛይንና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ የደቡብ መስኖ ባለሥልጣንና የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት