የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የ1ኛ ዓመት ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ ኮሌጁን መርጠው አዲስ ለተቀላቀሉ የ2 ዓመት ተማሪዎች የእንኳን ደኅና መጣችሁ አቀባበል እንዲሁም በ2014 ዓ/ም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ የ 3 እና የ4 ዓመት ተማሪዎች የሽልማት መርሃ ግብር አካሂዷል፡፡

የኮሌጁ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ መርሃ ግብሩ ወደ ኮሌጁ የተቀላቀሉ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ከት/ክፍል ኃላፊዎች ጋር ለማስተዋወቅና በ2014 ዓ/ም የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የ3 እና የ4  ዓመት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ለማበርከት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመርሃ ግብሩ ከየት/ክፍሉ ሁለት ሁለት ተማሪዎችና  በኮሌጅ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ አንድ ወንድና አንድ ሴት በድምሩ ሁለት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት የተበረከተላቸው መሆኑን ዲኑ ገልጸዋል፡፡ ትውውቁ ተማሪዎቹ የሚኖራቸው የትምህርት ቆይታ የተሳለጠ እንዲሆን የሚረዳ ሲሆን የሽልማት መርሃ ግብሩም ተሸላሚዎቹን ለተሻለ ሥራ የሚያበረታታና ተከታዮቻቸውም በትምህርታቸው እንዲተጉ የሚያነሳሳ እንደሆነ ዶ/ር መስፍን ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎቹ በሚኖራቸው ቆይታ ጠንካራና ተወዳዳሪ በመሆን ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው ብሎም ለሀገር ጠቃሚ ዜጋ መሆን እንደሚገባቸው ዲኑ አሳስበዋል፡፡

ከየትምህርት ክፍሉ የተገኙ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ስለትምህርት ክፍሎቻቸውና የትምህርት ሂደት ገለጻና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የኮሌጁ አመራሮች፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ መምህራንና ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት