የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል ‹‹የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አሠራር፣ የሚዲያ አተገባበርና ንቃት›› በሚል ርዕስ ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መጋቢት 30/2015 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ዓለማየሁ  ሥልጠናው በዋናነት ተማሪዎች የፐብሊክ ዲፐሎማሲን ምንነትና አሠራር እንዲሁም የሚዲያውን አተገባበር ተገንዝበው በተለያዩ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መልዕክቶችን በሰላ ዕይታ መመርመር እንዲችሉና ራሳቸውን ከአላስፈላጊ የሚዲያ ተጽዕኖ ነፃ እንዲያደርጉ ግንዛቤን ለማስጨበጥ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከአሠልጣኞች መካከል የዩኒቨርሲቲው የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ት/ክፍል መምህር ዶ/ር ይሄነው ውቡ "The Structure and Elements of Public Diplomacy During the Recent War in Northern Ethiopia "በሚል ርዕስ ባቀረቡት ሠነድ እንደገለጹት ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ኢትዮጵያ ውስጥ በተጠና ሁኔታ ባይተገበርም የተለያዩ ሀገራዊ ችግሮች ሲከሰቱ ችግሮቹን ለመፍታት ፐብሊክ ዲፕሎማሲን እንደ አንድ የዲፕሎማሲ ዘርፍ ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረግ ጥረት ተስተውሏል፡፡ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማለት በሌሎች ሀገራት ያሉ ማኅበረሰቦች ስለ እኛ ምን ያስባሉ የሚል ሲሆን አሁን ላይ በሀገራችን  ውስጣዊ ችግርና ውጫዊ ከፍተኛ ተፅዕኖ ምክንያት በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ዶ/ር ይሄነው ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ በአደጉት ሀገራት እንደ ሚዲያ፣ ባህል፣ ቋንቋና የመሳሰሉትን ዘዴዎች  ለፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንደሚጠቀሙ አሠልጣኙ ጠቀመዋል፡፡

ሌላኛው አሠልጣኝ የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ት/ክፍል መምህር ተመስገን ካሰ በበኩላቸው “Changing Climate of Media” በሚል ርዕስ በቀረቡት ጽሑፍ ሚዲያ ሊትረሲ /Media Literacy/ የሚዲያን አሠራር የመመርመርና በዜናም ሆነ በመዝናኛ መልክ የሚተላለፉ መልዕክቶችን እንዲሁ ከመቀበል ባሻገር “ለምን?” እና “እንዴት?” የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት በሰላ ዕይታ የመመልከት አቅምና ግንዛቤ ነው ብለዋል፡፡  ተማሪዎች ሀገራዊ አንድነትን ለማጎልበት የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም የሀገራቸውን እውነታ ለማሳወቅ ጥረት ማድረግና የሚቀበሉትንም መልዕክት በተረጋጋ አዕምሮና በማስተዋል እንዲሁም ከስሜታዊነት ይልቅ በምክንያታዊነት ቢጠቀሙት መልካም መሆኑንም አሠልጣኙ አሳስበዋል፡፡

በፕሮግራሙ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቷባቸዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት