በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግራንትና ኮላቦሬቲቭ ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት የምርምርና የትብብር ፕሮጀክቶች ግምገማ ሚያዝያ 10/2015 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የትብብር ፕሮጀክቶች ለሀገር ልማት፣ ለማኅበረሰብ ኢኮኖሚ መሻሻል እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ለመሆን እያደረገ ካለው ቅድመ ዝግጅት ጋር ተያይዞ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው እንደ ተቋም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ የሚገኝ እንደመሆኑ መምህራንና ተመራማሪዎችም ፕሮጀክቶችን ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በበኩላቸው ፕሮጀክቶቹ ሲቀረጹ ከተሰጣቸው ዓላማ አንጻር ያከናወኗቸው ተግባራት፣ ከዩኒቨርሲቲው ራእይና ተልእኮ አንጻር ያላቸው አስተዋጽኦ፣ ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት ሚኒስቴርና ለሌሎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በሚያደርገው ሪፖርት ውስጥ ክንውኖቹ መካተት አለመካተታቸው እንዲሁም እያንዳንዱ ፕሮጀክት በግል ያበረከተው አስተዋጽኦ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የግምገማ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው 30 የሚሆኑ የምርምርና ትብብር ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የተናገሩት የግራንትና ኮላቦሬቲቭ ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶማስ ቶሮራ ከፕሮጀክቶቹ መካከል በአግባቡ ተመዝግበው የሚታወቁት 16 ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ተገምግመው አያውቁም ብለዋል፡፡ መድረኩ ፕሮጀክቶቹ ያሉበትን አቋም፣ የሠሯቸውን ተግባራት፣ ጠንካራና ደካማ ጎኖቻቸውን እና በቀጣይ መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ በቀረበው ሪፖርት መሠረት ተገምግመው በዩኒቨርሲቲው ደረጃ የራሳቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት አቋም ላይ እንዲደርሱ ለማስቻል የሚረዳ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ከፕሮጀክቶቹ አንዱ የሆነው ‹‹Adoption of Rhizobium Inoculant Technology›› ፕሮጀክት ፈረንሳይ ሀገር ከሚገኝ ‹‹Fund for Innovative Development (FID) ከተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ጋር በትብብር የሚሠራና በአፈር ውስጥ የናይትሮጅን ንጥረ ነገርን መጠን በሚወስኑ ባክቴሪያዎች ዙሪያ ጥናት የሚያካሂድ ሲሆን ባክቴሪያዎቹን ከአፈር ውስጥ ለይቶ በማውጣት በቂ የናይትሮጅን ንጥረ ነገር መጠን እንዲኖር የሚያስችሉ ፓኬጆችን በላቦራቶሪ አዘጋጅቶ ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት የአፈር ንጥረ ነገር በመጨመር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሠራ መሆኑን የፕሮጀክቱ አቅራቢ በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር አሸናፊ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡

‹‹ASTU-AMU One Tone Fish Production››፣ ‹‹Bright Future in Agriculture-South, South Ethiopia››፣ ‹‹Network of Universities in Public Health (SENUPH II)››፣ ‹‹Innovative Enset Project››፣ ‹‹Pico-Hydropower Dingamo Project››፣ ‹‹Adoption of Rhizobium Inoculant Technology›› እና ‹‹The Rural-Urban Nexus Establishing a Nutrient Loop to Improve City Region Food System Resilience (RUNRES) Project›› ለግምገማው ከቀረቡ የምርምርና የትብብር ፕሮጀክቶች መካከል ጥቂቶቱ ናቸው፡፡

በግምገማው የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና ተመራማሪዎች የተገኙ ሲሆን የ16 ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ቀርቦ ተገምግሟል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት