አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአየር ለውጥ ምክንያት በሚከሰት የድንች ምርት መቀነስ ዙሪያ የሚሠራ የ1.13 ሚሊየን ብር ግራንድ የምርምር ፕሮጀክት ሚያዝያ 11/2015 ዓ/ም ይፋ አድርጓል፡፡  ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ቶማስ ቶሮራ እንደገለጹት በወረዳዎቹ የአየር ጠባይ መለኪያ መሣሪያ በማስቀመጥ መለካት፣ የምርምር ውጤቶችን መሠረት በማድረግ የድንች እድገትና ምርት ላይ ተጽእኖ የሚያደርሰውን የአየር ጠባይ በመለየት የዘር ጊዜ መቀየር፣ አረምና በሽታን መከላከል፣ የአየር ጠባይ ሊቋቋሙ የሚችሉ ዝርያዎችን ለይቶ ማስቀመጥና የመሳሰሉ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ መፍጠር የፕሮጀክቱ ግቦች ናቸው፡፡ ዶ/ር ቶማስ በገለጻቸው የአየር ጠባይ፣ የድንች ዘር፣ የመሬት ሁኔታና የሰብል አያያዝ የድንች ምርታማነትን የሚወስኑ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም ፕሮጀክቱ የግብርና፣ የአየር ንብረትና ውኃ ዘርፎችን የሚያስተሳስር መሆኑን ጠቅሰው የየዘርፉ ባለሙያዎች ንቁ ተሳትፎ ለስኬቱ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የውኃ ሀብት ምርምር ማእከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሙኤል ዳጋሎ በበኩላቸው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ወቅቱን ጠብቆና ናሙና ላይ መሠረት አድርጎ ዘር በመዝራት ጥሩ ውጤት ለማምጣትና በአየር ለውጥ ምክንያት የሚከሰተውን የምርት ማነስ ችግር ለመፍታት ከአርሶ አደሩ ጋር ተቀራርቦ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ተመራማሪና በሆርቲካልቸር ትምህርት ዘርፍ የ3 ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ዕጩ ዶ/ር ፈቃዱ ንጋቱ በፕሮጀክቱ አማካኝነት የሚሰበሰበው መረጃ ለምርምር ሥራቸው በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ድንች ቶሎ የሚደርስ፣ በርካታ የምግብ ንጥረ ነገሮችን የያዘ፣ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ ብሎም የደጋው አርሶ አደሮች የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆኑ የአየር ለውጥ ተጽእኖን መቋቋም የሚችል የድንች ዘርና የሚተከልበትን ወቅት በመለየት አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ግንዛቤን የመፍጠር ኃላፊነት አለብን ብለዋል፡፡

የፕሮጀክቱ አባል የሆኑት አቶ ካንኮ ጩታላ በበኩላቸው በተሰጠው ገለጻ በፕሮጀክቱ ለሚሠራው ምርምር በባለሙያዎች በየቀኑ የሚወሰዱ የአፈር ናሙና፣ ሰብሉ የበቀለበት ቀን፣ የአበባና ድንቹ ያኮረተበት ቀን መዝግቦ የመያዝና የምርት አሰባሰብ መረጃን አስመልክቶ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ የጨንቻ፣ ቆጎታ፣ ጋጮባባ እና ቦንኬ ወረዳዎች የሰብል ጥበቃ ባለሙያዎችና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ተመራማሪዎችና ምሁራን እንዲሁም የ2ኛ ዲግሪ ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡

 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት