የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ "Jhpiego" ጃፓይጎ ከተሰኘ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በትብብር እየሠራ ሲሆን በትብብር ሥራው የእስከ አሁን አፈፃፀምና ቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን በተመለከተ ሚያዝያ 23/2015 ዓ/ም በአካዳሚክ ጉ/ም/ፕ/ጽ/ቤት ምክክር ተደርጓል፡፡ ፎቶዎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በጃፓይጎ "Health Workforce Improvement Program" የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ ፕሮግራም ማኔጀር አቶ አስፋው ደምሴ እንደገለጹት ጃፓይጎ ከአሜሪካው ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር የሚሠራና የጤና ሥርዓትንና የማኅበረሰብ ጤናን ማጠናከርን ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡ ድርጅቱ "Health Workforce Improvement" በተሰኘው ፕሮግራሙ የጤና ባለሙያዎች ትምህርት ላይ እያሉ ተገቢውን ክሂሎትና አመላካከት አግኝተው እንዲወጡ የሚያስችሉ ለመምህራን የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ የተግባር ትምህርትን በማጠናከር፣ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ድጋፎችን በማድረግ እንዲሁም ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ አሠራሮችን በማጋራት ላይ አተኩሮ በትብብር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ አስፋው ገለፃ ድርጅቱ እ.አ.አ ከ2020 ጀምሮ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅን ጨምሮ 29 ሕክምናና ጤናን የሚያስተምሩ ተቋማትን እየደገፈ ሲሆን በዚህም ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እንደ ሀገር የትምህርት ጥራት ካጋጠመው አደጋ ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት እንደ ጃፓይጎ ካሉ ድርጅቶች የሚደረጉ ድጋፎች ጠቀሜታቸው ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ በድርጅቱ ድጋፍ የተሰጡ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች፣ የውስጥ ፕሮግራም ግምገማዎች እንዲሁም ለኮሌጁ  ቤተ-ሙከራ የተደረጉ ድጋፎች የመማር ማስተማሩን ሥራ ከማሻሻል አንፃር በእጅጉ የሚጠቅሙ መሆናቸውን ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡ ኮሌጁ የሥርዓተ-ትምህርቶች አተገባበርን ለመቆጣጠር የዲጂታል ፕላትፎርም በማዘጋጀት ተግባራዊ ለማድረግ ሙከራ ላይ መሆኑ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ዓለማየሁ  ፕላትፎርሙ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የራሱን ሚና ሊወጣ የሚችል በመሆኑ ሌሎችም የዩኒቨርሲቲው ኢንስቲቲዩቶች፣ ኮሌጆችና ት/ቤቶች ከኮሌጁ ተሞክሮ በመውሰድ ጭምር ልምዱን ለማስፋት ሊሠራ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ ኮሌጁ ከጃፓይጎ ጋር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ብሎም ብቃት ያላቸው የሕክምናና ጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው ይህም ኮሌጁ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ በድርጅቱ በተደረገ ድጋፍ በኮሌጁ የሚገኙ አምስት ፕሮግራሞች የውስጥ ግምገማ መደረጉን የተናገሩት ዶ/ር ታምሩ በግምገማው የተገኙ ክፍተቶች ላይ ማስተካከያዎችን በማድረግ ፕሮግራሞቹ በሀገር አቀፍ ደረጃ አክሪዲቴሽን (Accreditation) እንዲያገኙ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ኮሌጁ የመማር ማስተማር፣ የቁጥጥርና  የምዘና ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ዶ/ር ታምሩ ጠቁመዋል፡፡

የኮሌጁ ተቋማዊ ጥራት ማጎልበቻ ማ/ጽ/ቤት አስተባባሪ መ/ር አብነት ገ/መስቀል በበኩላቸው በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ተማሪዎች ውጤታማ ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጡ የብቃት መመዘኛ ፈተናዎችን በብቃት ማለፍ የሚችሉት በሚማሩበት ፕሮግራም ያለው ሥርዓተ-ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ኮሌጁ ሥርዓተ-ትምህርቶች በአግባቡ መተግበራቸውን ለመቆጣጠር የሚያስችል "Academic Performance Monitoring" የተሰኘ ፕላትፎርም በማበልጸግ በቅርቡ የሙከራ ሥራ እንደሚጀምር ጠቁመዋል፡፡ ፕላትፎርሙ በኦንላይን የሚሠራ ሲሆን በሥርዓተ-ትምህርቶቹ ውስጥ የተካተቱ ተግባራት መተግበራቸውን ከተማሪዎች በኦንላይን በሚሞላ ፍርም መሠረት መቆጣጠር የሚያስችል እንደሆነም አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡ ይህም የታዩ ድክመቶች ላይ በአፈጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የሚያግዝ ሲሆን ፕላትፈርሙ ከ2016 ዓ/ም ጀምሮ በኮሌጁ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት