የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታዳሽ ኃይል ምርምር ማእከል በእንግሊዝ ሀገር ከሚገኙት "Crop Health and Protection /CHAP/" እና "Space and Water Solutions Ltd/LENKE/ "የተሰኙ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ‹‹Optimizing Energy Demand in Rural Communities via Precision Agriculture Technology/SWIFT/›› የተሰኘ አዲስ የትብብር ፕሮጀክት በጋርዳ ማርታ ወረዳ ሚያዝያ 18/2015 ዓ/ም ይፋ አድርጓል፡፡ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅ/ጉ/ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ በኢትዮጵያ ብሎም በመላው አፍሪካ በምግብ ራስን የመቻል ሥራ ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከያዘችው አጀንዳ አንጻርም ፕሮጀክቱ ማኅበረሰብ አቀፍና አንድ እርምጃ ቀዳሚ ነው ብለዋል፡፡ በአካባቢው ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በነበረው የዝናብ እጥረት ምክንያት ያጋጠመውን የምግብ እጥረት ችግር ለማቃለል ዩኒቨርሲቲው የተቻለውን እገዛ ማድረጉን የጠቀሱት ም/ፕሬዝደንቱ የጉድጓድ ውኃን በማጎልበት ለማኅበረሰቡ አገልግሎትና ለመስኖ እንዲውል ለማድረግ ፕሮጀክት ቀርጾ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የምርምር ዋና ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ አካባቢዎች የትብብር ፕሮጀክቶችን በመሥራትና በማስተዳደር ልምድ ያካበተ መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበት አካባቢ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች አመቺ የሆኑ ከፍተኛና ዝቅተኛ ቦታዎችን ያቀፈ መሆኑ ለአግሮኢኮሎጂ ሥራዎች ተመራጭ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ኃይልን በተመለከተ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተቋቋመ ማእከል መኖሩን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ ይፋ የተደረገው የትብብር ፕሮጀክት በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የታዳሽ ኃይል ምርምር ማእከል ተመራማሪና የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ አቶ በየነ ፈዬ ፕሮጀክቱ አካባቢዎቹን የመስኖ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚሠራ መሆኑን ገልፀው የፕሮጀክቱ ቡድን ተዘዋውሮ ምልከታ ካደረገባቸው ቦታዎች አንጻር ጋርዳ ማርታ ከከተማና መሠረተ ልማቶች የራቀ በመሆኑ የአካባቢው አርሶ አደሮች መሬትና ውኃ እያላቸው ለድርቅ መጋለጣቸውንና ከብቶቻቸውም መጎዳታቸውን ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ማእከሉ ከሁለቱ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ፕሮጀክቱን ማስጀመሩን ያወሱት አስተባባሪው ለፕሮጀክቱ ትግበራ ከእንግሊዝ መንግሥት (Innovative UK) £279,132 የእንግሊዝ ፓውንድ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል አካባቢውን የኤሌክትሪከ ኃይል ተጠቃሚ በማድረግ አርሶ አደሩ በፊት ሲጠቀምበት የነበረውን የነዳጅ ወጪ መቀነስ፣ የማገዶ እንጨትን በመጠቀም የሚመጣውን የሴቶች የሥራ ጫናና የአየር ንብረት ለውጥ መቀነስ እና አርሶ አደሩ አስፈላጊውን የሰብል ቴክኖሎጂ በመጠቀም ውኃን ወደ ማሳው ፓምፕ አድርጎ በመስኖ እንዲያመርት ማስቻል እንደሚጠቀሱ አቶ በየነ ተናግረዋል፡፡

የ"Crop Health and Protection/CHAP/" ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ልማት ድርጅት ማኔጀር ዶ/ር ጄና ሮስ (Jenna Ross) ድርጅታቸው በዋናነት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚሠራ መሆኑን ተናግረው ከተለያዩ ኢንደስትሪዎች፣ የቢዝነስ፣ የምርምርና የትምህርት ተቋማት ጋር ምርትን ማሳደግ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለማበልጸግ በትብብር ይሠራል ብለዋል፡፡ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት ከተቋሙ ዓላማ ጋር አብሮ የሚሄድና የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈታ በመሆኑ ተቋማቸው ለፕሮጀክቱ መሳካት የሚጠበቅበትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ዶ/ር ጄና ገልጸዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አስተዳደራዊ ሥራዎችንም በዋናነት ድርጅታቸው እንደሚያከናውን ማኔጀሯ ተናግረዋል፡፡

የ"Space and Water Solutions Ltd/LENKE" መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሌንሳ ኢተፋ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ አመቺ ለሆነ የውኃ ኃይልና ለተሻለ የሰብል ምርት አጋዥ ሆኖ መቅረቡን ገልጸው በየትኛውም ቦታ ሊተገበር የሚችልና ለማኅበረሰቡ ቁልፍ ሚና ያለው ነው ብለዋል፡፡ ድርጅቱ በዋናነት የሳተላይት ምስል መረጃ በመተንተን የማረጋገጥ ሥራና ሌሎች ተያያዝ ጉዳዮችን እንደሚያከናውን ዶ/ር ሌንሳ ገልጸዋል፡፡

የጋርዳ ማርታ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ አጅሬ በበኩላቸው እንደገለጹት በአካባቢያቸው ሰፊ መሬትና ውኃ ያለ ቢሆንም ከ2012 ዓ/ም ጀምሮ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ስድስት የምርት ዙሮችን በዝናብ እጥረት በተፈጠረ ድርቅ ምክንያት ያጡ ሲሆን የአካባቢው ማኅበረሰብ ከኤሌክትሪክ ኃይል የሚገኙ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ዕድልም ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ ፕሮጅክቱ አካባቢው ካለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አኳያ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ ይሠራል ብለን ተስፋ እናደርጋለንም ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የታዳሽ ኃይል ምርምር ማእከል ዳይሬክተር አቶ ሶዴሳ ሶማ ማእከሉ ከዚህ ቀደም የሰሃይ ሶላርና የባዮጋዝ ታዳሽ ኃይል አማራጭ ቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶችን ለዞኑ ገጠራማ አከባቢዎች በብቃት የማዳረስና የማስፈጸም ልምድ ያካበተ እንደመሆኑ ይህንንም ፕሮጀክት የተሳካ ለማድረግ ይሠራል ብለዋል፡፡

ለፕሮጀክቱ አጠቃላይ በጀት £279,132 የእንግሊዝ ፓወንድ የተመደበለት ሲሆን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ 35,625 ፓወንድ ወይም በብር 2,417,512.50፣ “Crop Health and Protection /CHAP/” £73,501 ፓወንድ ወይም ብር 4,987,777.86 እና “LENKE Space and Water Solutions Ltd” £170.006 ፓወንድ ወይም ብር 11,536,607.16 በየድርሻቸው የሚሸፍኑ ይሆናል፡፡ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 650 ሄክታር መሬት መስኖ ለማልማት የሚያስችልና በአካባቢው የሚገኙ ከ400 በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ ፕሮጅክቱ  ከሚያዚያ 1 2015 ዓ.ም እስከ መጋቢት 21/ 2016 ዓ.ም ድረስ የሚቆይና በአንድ ዓመት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የታቀደ ነው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት