በወባ በሽታ መከላከልና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ እየሠራ በሚገኘው “AMU-SENUPH II” ፕሮጀክት የወባ በሽታን ለመከላከል በጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያና ምዕራብ ዓባያ ወረዳዎች በተመረጡ ቀበሌዎች ቤቶችን በማሻሻል እና የአይቨርሜክቲን (Ivermechtin) የከብት ህክምና (House Screening and Ivermechtin Cattle Treatment) በወባ ስርጭት ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመረዳት የመስክ ትግበራ ለመጀመር የሚያስችል ውይይት ከባለድርሻዎች ጋር ሚያዝያ 18/2015 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ መምህር፣ ተመራማሪ እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ፍቃዱ ማሴቦ ኬሚካል በመርጨት፣ አጎበር በመጠቀም፣ ያቆረ ውኃ በማፍሰስና ሕክምናን በመጠቀም ለበርካታ ዓመታት የወባ በሽታ ስርጭትና በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ቀንሶ የነበረ ቢሆንም ካለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ ስርጭቱ እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት ተጨማሪ  መከላከያ ዘዴዎች ላይ ጥናቶችን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ አስተባባሪው ማብራሪያ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቀነስና ችግሮችን በማወቅ ለመከላከል የሚያስችሉ ምርምሮችንና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግ የወባ ትንኝ የሰው ደም እንዳይመገብ ማድረግና ትንኞች ከብቶች ላይ በመሆን ሕይወታቸውን እንዳያቆዩ ከብቶችንም ማከምና የአጎበር አጠቃቀምን ማሻሻል እንዲሁም የወባ በሽታ እንዲጨምር የሚያደርጉ ነገሮችን መቀነስ የፕሮጀክቱ ግቦች ናቸው፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በወረዳዎቹ በተመረጡ ቀበሌዎች በተመረጡ ቤቶች ላይ ናሙና በመሥራት የወባ ትንኝና የወባ በሽታ ምን ያህል እንደቀነሰ፣ ውጤታማነቱንና ማኅበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነትና የማስቀጠል ፍላጎት በፕሮጀክቱ የሚተገበሩ መሆኑን ዶ/ር ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከምርምሩ ባሻገር በርካታ የ3ና የ2 ዲግሪ ተማሪዎችን እንደሚደግፍም አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የላንቴ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ፍቅረአብ ደንበል እንደገለጹት የወባ በሽታን ለመከላከል ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን የወባ በሽታ ትንኝ ወደ ቤት እንዳይገባና በውጪም እንዳይራባ ምቹ ሁኔታዎችን ማጥፋት፣ ከብቶችን ማከም እና መሰል ተግባራት ቢከናወኑ ጥሩ ውጤት ማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሚደረገው ምርመር የወባ በሽታ ስርጭትን በከፍተኛ ደረጃ የመቀነስ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት