የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ከአርባ ምንጭ ከተማ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳዮች ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከከተማው አስተዳደር ለተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎች የአመራርነት ሥልጠና ግንቦት 4/2015 ዓ/ም ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ማኅሌት ደፈርሻ ለሀገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት የሁሉም ኅብረተሰብ ክፍል የነቃ ተሳትፎ አስፈላጊ በመሆኑ የሴቶችን የነቃ ተሳትፎ በሁሉም ዘርፍ ማጎልበት ይገባል ብለዋል፡፡ በሀገራችን የሴቶች ቁጥር ከአጠቃላይ ሕዝብ ብዛት ከግማሽ በላይ ቢሆንም በቁጥራቸው ልክ ተሳታፊና ተጠቃሚ እየሆኑ አለመሆኑን የጠቆሙት ኃላፊዋ የሴቶች ውሳኔ ሰጪነትን የሚያጎለብቱ ሁኔታዎችን መፍጠር ላይ ጽ/ቤታቸው በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አስተባባሪ ወ/ሮ አስቴር ሰይፉ ኮሌጁ በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ ከሴቶችና ሕጻናት ዘርፍ ጋር የተገናኙና ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የሴቶችን የውሳኔ ሰጪነት አቅም ማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤን በማጎልበት የአመራርነት ሚናቸውን በውጤታማነት እንዲወጡ ማስቻል ሥልጠናው የተዘጋጀበት ዓለማ መሆኑንም አስተባባሪዋ ገልጸዋል፡፡

የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መ/ርና አሠልጣኝ አበበ ዘየደ ሥልጠናው የአመራርነት ጥበብን የሚያዳብር በመሆኑ በአቅም ማነስ የሚፈጠሩ ግድፈቶችንና  የደንበኛ መጉላላትን ለማስቀረት ይረዳል ብለዋል፡፡

ሌላኝዋ አሠልጣኝ መር/ት ብርቱካን ላመስግን ሴቶች አመራርነትን የሚጀምሩት ከታች ከእናታቸው ጓዳ እንደሆነ ጠቅሰው ያላቸውን የቀደመ ግንዛቤና ከሥልጠናው የሚያገኙትን ዕውቀት በማዋሃድ በሚሠሩበት ቦታ የተሻለ ዕውቀት በመያዝ በራስ መተማመናቸውን ለማጎልበት ይረዳል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በሀገራችን ሴቶች ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ በመሆኑ በሥልጠናው የራሳቸውንና የሚያገለግሉበትን ድርጅት የአመራርነት ብቃት እንደሚያዳብር ተናግረዋል፡፡

ከሠልጣኞች መካከል የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ጽ/ቤት የልማት ዕቅድ ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ቆንጂት ኃ/መስቀል መሰል የማነቃቂያ ሥልጠናዎች በየወቅቱ መሰጠት ቢችሉ በሴቶች ላይ  መነሳሳትን የሚፈጥሩና  የአልችልም ስሜት በማስቀረት ለሥራ የሚያነቃቁ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የአመራር ምንነት፣ የሠራተኛን ስሜት በአስተውሎት መረዳትና ማስተዳደርና ሌሎች ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች የሥልጠናው ትኩረት ናቸው፡፡ በሥልጠናው ከ22 ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የተወጣጡ ሴት የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት