አርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት 4ኛውን ‹‹የምኅንድስናና ቴክኖሎጂ ፈጠራና ተግዳሮቶች ለዘላቂ ልማት/ Innovation and Challenges in Engineering and Technology for Sustainable Development (ICET-2023)›› ዓመታዊ ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ከግንቦት 18-19/2015 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዙህ ይጫኑ፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትና የፕሬዝደንት ተወካይ ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርምሮችን በአግባቡ ከሠሩ የማኅበረሰቡን ችግር በመፍታትና አኗኗሩን በማሻሻል ለሀገር አመርቂ ውጤት እንደሚያስገኙ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንጻር አርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከሚሠራቸው ምርምሮች ባሻገር በገጠራማ አካባቢዎች ላሉ ት/ቤቶችና ጤና ተቋማት የፀሐይ ታዳሽ ኃይል በመዘርጋት፣ የውኃ መስመርና ድልድዮችን ዲዛይን በመሥራትና ለሕንፃ ግንባታ የአፈር ጥናት በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

የአርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉነህ ለማ በበኩላቸው ኮንፍረንሱ መዘጋጀቱ ተመራማሪዎች የሚሠሩትን የምርምር ሥራ እንዲያቀርቡ እድል ይሰጣል ብለዋል፡፡ በኮንፍረንሱ 17 ኢንስቲትዩቶች የተሳተፉ ሲሆን 14 ዩኒቨርሲቲዎች ከኢትዮጵያ፣ ሁለቱ ከአፍሪካ መሆናቸውን እና በምኀንድስናና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሠሩ 20 ጥናታዊ ጽሑፎች መቅረባቸውን ዶ/ር ሙሉነህ ገልጸዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ የራሱን “Ethiopian International Journal Engineering & Technology/EIJET” የተሰኘ ጆርናል ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳተመበት ዓመት መሆኑ አውደ ጥናቱን ታሪካዊና ልዩ የሚያደርገው መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሙሉነህ የምርምር ጆርናሉ በኢንጂነርንግና ቴክኖሎጂ፣ በአዳዲስ የኢነርጂ ዘርፎች እና ሌሎች ተያያዥ መስኮች የተከናወኑ ጥናታዊ ጽሑፎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚታተሙበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም ላለፉት ሦስት ዓመታት ኮንፍረንሱ በኢንስቲትዩቱ ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰው ኮንፍረንሱ በዋናነት የምርምር ውጤቶችን ለሌሎች ለማስተዋወቅና በምኅንድስና ዘርፍ የሚሠሩ ምርምሮችን በጋራ ለመሥራት ልምድ ልውውጥ የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሜሪካ ሀገር በሚገኘው Microsoft ተቋም ዋና የሶፍትዌር መኀንዲስና የዳታ ሳይንቲስት/Principal Software Engineer and Data Scientist/ ዶ/ር ደነቀው አበራ ‹‹Information Communication Technology and Computing System for Sustainable Development›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ቁልፍ መልዕክት መረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ለትምህርት፣ ለምርምር፣ ለመንግሥታዊ ሥራዎችና ለንግድ ሥርዓት ያለውን ፋይዳ እንዲሁም ገጠርና ከተማን በተመሳሳይ ደረጃ በመረጃ ልማት ማገናኘትን አስመልክቶ በስፋት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሌላኛው ቁልፍ መልዕክት አቅራቢ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማትና ምኅንድስና ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዳንኤል ሊሬቦ ፈጠራን በማጎልበት የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚናቸው ከፍ ያለ ሲሆን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በምኀንድስናው ዘርፍ በዕውቀትና በክሂሎት የታነፁ በርካታ ባለሙያዎችን በማፍራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የእንሰት አመራረት ሂደትን ለማዘመን የሠራቸው ምርምርና ቴክኖሎጂዎች የሚደነቁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ቴክኖሎጂና ፈጠራን ማሳደግ የማይችሉ ባለሙያዎችን ማስመረቅ ከዘርፉ ተግዳሮቶች አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ዳንኤል ለውጥ ለማምጣት ዩኒቨርሲቲዎች በአዲስ መልክ ምርምሮችን ማጠናከርና የተሻለ ጥራት ያለው ትምህርትን ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ከቀረቡ ምርምሮች መካከል አንዱ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዲን ዶ/ር ዘውዴ ሞስኤ “Pulmonary Disease Identification and Classification Using Deep Learning Approach” በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጥናት ሲሆን በጥናታቸውም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚጻፉ የሰው ሀሳብ የሚገልጹ ጽሑፎች የሕዝብ ስሜት ምን ይላል የሚለውን በአጭሩ ማጠቃለል የሚችሉ ማሽኖችን በማሠልጠን በብዛት የሚገኘውን ጽሑፍ በየዘርፉ የሚያስቀምጥ ሞዴል የተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የጥናቱ ዋና ዓላማ በርካታ የምንለውን መረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለምንፈልገው አካል ጠቅለል አድርጎ መስጠት ሲሆን በቴክኖሎጂ እያደገ በመጣው በዚህ ዘመን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ሌላኛው ተመራማሪ መ/ር አሚን ቱኒ የኮንሶ ሕዝብ የአፈር ጥበቃ ዘዴን ከሀገር በቀል የዕውቀት አመራር ማዕቀፍ ማሰስ እና መንደፍ በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የምርምር ግኝታቸውን ያቀረቡ ሲሆን በዚሁ ግኝት መሠረት የሀገር በቀል ዕውቀት አስተዳደር ወይም አመራር ማዕቀፍ እና የተሻሻለው ፕሮቶታይፕ በዘርፉ ያለው  የዕውቀት አመራር ሂደትን ቀላልና ቀልጣፋ እንዳደረገው አብራርተዋል፡፡  አቅራቢው ግኝታቸው በኮንሶ አካባቢ ላለው ማኅበረሰብ ቀደም ሲል ለልማት ሥራዎች ታቅዶ ላለው የአይ.ኤም.ኤም/IMM/ ማዕቀፍ የላቀ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ተመራማሪው በኮንሶ አካባቢ ያጠነጠነውን ግኝትንና መሰል የሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍና ማቆየት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በኮንፍረንሱ ከቀረቡ ምርምሮች መካከል ‹‹Pulmonary Disease Identification and Classification Using Deep Learning Approach››፣ ‹‹Exploring and Designing Indigenous Knowledge Management Framework for Konso Peoples Soil Conservation Mechanism››፣ ‹‹Numerical Investigation of Reinforced Concrete Beam Containing Iron Ore Tailings as Partial Replacement of Sand›› እና ‹‹Biomimetic Architecture an Innovative Approach to Attain Sustainability in Built Environment›› የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በዓውደ ጥናቱ 17 ኢንስቲትዩቶች የተሳተፉ ሲሆን 14 ዩኒቨርሲቲዎች ከኢትዮጵያ፣ ሁለት ከአፍሪካና 1 ከምርምር ኢንስቲትዩት የተሳተፉ ሲሆን በምኀንድስናና በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተሠሩ 20 ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ 

በመርሃ ግብሩ መጨረሻ ለጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢዎችና ለአዘጋጅ ኮሚቴዎች የተሳትፎ እንዲሁም ለ“OVID KLING CONSULT” እና “QTC Engineering Consultancy PLC” ካምፓኒዎች በፕላቲኒየምና በብር ደረጃ ሲምፖዚየሙን ስፖንሰር በማድረጋቸው የምስክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

 

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

For more Information Follow us on:-
Website - https://www.amu.edu.et/
Telegram - https://t.me/arbaminch_university
Facebook - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
YouTube - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት