የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚገኙ ሁለት መቶ አካል ጉዳተኛና ችግረኛ ተማሪዎች መስከረም 25/2016 ዓ/ም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አብዛኛውን ጊዜ የትምህርት መግቢያ ወቅት ለወላጅና አቅም ለሌላቸው ፈታኝ ወቅት መሆኑን ተናግረው ድጋፉ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ የሚያግዛቸው አካል ከጎናቸው መኖሩን እንዲያስቡ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡ በየደረጃው ያሉ ችግሮችን እንደ ባህላችን በመተጋገዝና በመደጋገፍ ማለፍ ይገባናል ያሉት ፕሬዝደንቱ ውጤታማ ለመሆን ከድጋፉ ባሻገር የራስ ጥረት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ መኩሪያ በበኩላቸው በድጋፉ 210,000 (ሁለት መቶ አሥር ሺህ) ብር ወጪ በማድረግ ለሁለት መቶ ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው 12 ደብተርና 10 እስክሪብቶ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክቶሬታቸው በየዓመቱ በዕቅድ ከሚሠራቸው ሥራዎች አንዱ በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መደገፍ ነው ያሉት አቶ መርክነህ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፉ የነገ ሀገር ተስፋ የሚሆኑ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳያቋርጡ ታስቦ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ ዩኒቨርሲቲው በከተማዋና በዙሪያዋ በሚገኙ ት/ቤቶች ከሕንፃ ግንባታ ጀምሮ የቤተ ሙከራ፣ የቤተ መጻሕፍትና ሌሎች የውስጥ ቁሳቁሶች ድጋፍ እያደረገ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለአካል ጉዳተኛና ችግረኛ ተማሪዎች ላደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበር አባልና በዓባያ 2 ደረጃ ት/ቤት የ11 ክፍል ተማሪ አማረች አልቦ እና የ10 ክፍል ተማሪ ቴዎድሮስ አያሌው የትምህርት ቁሳቁስ በማጣት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ አስበው እንደነበር ገልጸው የተደረገልን ድጋፍ በትምህርታችን እንድንቀጥልና ጥሩ ውጤት በማምጣት በተራችን ሌሎች የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት እንድንችል አነሳስቶናል ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት