በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመተባበር 24 ሺህ ዶላር የተመደበለት ‹‹Assessment of Skin NTDs Burden through Community Screening during Scabies MDA Campaign in Gamo Zone›› በሚል ርእስ የሚሠራ የትብብር ፕሮጀክት መስከረም 28/2016 ዓ/ም ይፋ አድርጓል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ እንደገለጹት ትኩረት የሚሹ ቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ከምሥረታው ጊዜ ጀምሮ በሽታዎቹን ከመከላከልና ከማከም አንጻር ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ምርምሮችን ሲያከናውንና ሥልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በምርምር ማዕከሉም ሆነ በኮሌጅ ደረጃ ከአጋር ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ በማግኘት የሚደረጉ የምርምር ሥራዎች እያደጉ መምጣታቸውን የገለጹት ዶ/ር ታምሩ ይህም ከመንግሥት በጀት ጠባቂነት በመውጣት ምርምሮችን የማድረግ አቅም እየጎለበተ መምጣቱን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ይፋ የተደረገውና ከዓለም ጤና ድርጅት በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወነው የምርምር ፕሮጀክት ከዚህ አንጻር የሚጠቀስ መሆኑንም ዶ/ር ታምሩ ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በቆዳ ላይ የሚከሰቱ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን ስርጭት በመለየት በሽታዎቹ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጣቸው እንዲሁም በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር ሚናው የጎላ እንደሆነም ዶ/ር ታምሩ አውስተዋል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ኩሲያ እንደተናገሩት ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ተገቢውን ትኩረት ያላገኙ ነግር ግን በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የጤና፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውሶችን የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ በሽታዎቹን ለመከላከል እንዲሁም በበሽታው ለሚጠቁ ግለሰቦች ተገቢውን ሕክምና ለመስጠት እንደ ክልል ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ጥረቶች ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን ከዚህ አንጻር በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የምርምርና ሥልጠና ማዕከል ትልቅ እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ ማዕከሉ የሕክምና ባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት ረገድ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ሕክምናውን በቅርበት እንዲያገኝ የተወጣቸው ሚናዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ዳዊት ዩኒቨርሲቲው ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በመሆን በተለይ ቆዳ ላይ የሚከሰቱ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ላይ በማተኮር ሊያከናውን ያሰበው ሥራ ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ ያለው እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት ከተለዩ 22 ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች መካከል ዘጠኝ ያህሉ በቆዳ ላይ የሚከሰቱ ሲሆን እከክ፣ ሙጀሌ፣ ዝሆኔ፣ ቁንጭር/ቦልቦ/ እና ሌሎችም በሀገራችን በስፋት የሚስተዋሉ መሆኑን በምርምርና ሥልጠና ማዕከሉ ተባባሪ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዓለማየሁ በቀለ ጠቁመዋል፡፡ በሽታዎቹ የጤናና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ከማስከተላቸው ባሻገር በበሽታዎቹ የሚጠቁ ግለሰቦች በሚደርስባቸው መገለል ምክንያት ለከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ችግር እንደሚዳረጉም ተመራማሪው ጠቁመዋል፡፡

የምርምር ፕሮጀክቱ በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ በሚገኙ 14 ቀበሌያት የሚከናወን ሲሆን የበሽታ ልየታ ሥራው ለእከክ ከሚሰጠው ማኅበረሰብ አቀፍ የመድኃኒት እደላ ሥራ ጋር በማቀናጀት የሚከናወን መሆኑን አስተባባሪው አክለዋል፡፡ እንደ አስተባባሪው በቆዳ ላይ የሚከሰቱ ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታ ዓይነቶችና ሥርጭትን መለየት እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ የጤና ተቋማት በሽታዎቹን የመመርመርና የማከም አቅምን መፈተሽ የምርምር ፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓለማዎች ናቸው፡፡ የምርምር ሥራው የሚመለከታቸው አካላትን በማሳተፍ የሚከናወን ሲሆን የምርምሩ ውጤቶችም እንደ ሀገር በቀጣይ በመስኩ ለሚሠሩ ሥራዎች አቅጣጫ ጠቋሚና መነሻ ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉ አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በትብብርና በቅንጅት ለሚሠሩ እንዲሁም የማኅበረሰቡን ችግር ለሚፈቱ የምርምር ሥራዎች ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ይፋ የሆነው የምርምር የትብብር ፕሮጀክትም ከዚህ አንጻር ምሳሌ የሚሆንና ተመራማሪዎቻችን ከመንግሥት በጀት ባሻገር አጋሮችን በማፈላለግ መሥራት እንዳለባቸው የሚያሳይ ጥሩ ተሞክሮ እንደሚሆን ዶ/ር ተስፋዬ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ዩኒቨርሲቲው 60 ከመቶ ያህሉን የምርምር በጀት ወደ መሬት ወርደው ማኅበረሰቡን መጥቀምና ችግር መፍታት ለሚያስችሉ ግራንድ የምርምር ፕሮጀክቶች የሚመድብ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ በንግግራቸው አንስተዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች፣ መምህራን፣ የምርምር ቡድኑ አባላት፣ ከክልል፣ ዞን፣ ወረዳ እንዲሀም ከቀበሌ መዋቅር የተወጣጡ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት