የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የግራንትና የትብብር ፕሮጀክት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ለዩኒቨርሲቲው መምህራን በግራንት ንድፈ ሃሳብ አጻጻፍ ዙሪያ መስከረም 30/2016 ዓ.ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀብተማርያም ሥልጠናው  በግራንት ፕሮጀክት ውድድሮች ላይ አሸናፊ የሚያደርጉ የአጻጻፍ ክሂሎች ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ መምህራን በተገቢው መንገድ ተከታትለው ጥራት ያላቸው የግራንት ፕሮጀክት ንድፈ ሃሳቦችን በማዘጋጀት በውድድሮች አሸናፊ ለመሆን መሥራት እንደሚያሻ ገልጸው ያለውን የበጀት ችግር ለመቅረፍም ግራንት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ሁነኛ መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም አሸናፊ የሚያደርጉ የፕሮጀክት ንድፈ ሃሳቦች ሲጻፉ በዩኒቨርሲቲው በኩል የመነሻ ገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግና ፕሮጀክቶችንም ሲያሸንፉ ሽልማቶች እንደሚበረከቱ ጠቁመዋል፡፡

የግራንትና ትብብር ፕሮጀክት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶማስ ቶሮራ እንደገለጹት ለምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት በመንግሥት የሚመደበው በጀትና የሚደረግ ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ መምህራንና ተመራማሪዎች ማኅበረሰቡን ለማገልገል ውስንነት እንዲገጥማቸው አድርጓል፡፡ በመሆኑም እንደ ምርምር ዩኒቨርሲቲ ምርምሮችን ማካሄድና ማኅበረሰብን ማገልገል እንዲቻል መምህራንና ተመራማሪዎች የተሻሉ ፕሮፖዛሎችን በማዘጋጀት ውጪና ሀገር ውስጥ ለሚገኙ የተለያዩ ተቋማት በመላክ ገንዘብ እንዲያገኙና የዩኒቨርሲቲውን ተልእኮ በመደገፍ የተቋሙን ደረጃ ለማሳደግ ሥልጠናው ወሳኝ ግብዓት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በአሜሪካ ሀገር የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ቱፋ ድንቁ በመሠረታዊ የግራንት ፕሮጀክት ንድፈ ሃሳብ አጻጻፍ ምንነትና መስፈርቶች፣ ትክክለኛ ድጋፍ የሚያስገኙ ተቋማት ልየታና ትኩረት ሊደረግባቸው በሚገቡ ጉዳዮች እንዲሁም በንድፈ ሃሳብ ዝግጅት ወቅት አስቀድሞ ልኖር ስለሚገባው በቂ ዝግጅት ዙሪያ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ በውጪ ሀገራት ያሉ ተቋማትም ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት ፍላጎቱ ያላቸው መሆኑን ጠቁመው ይህም ገንዘብ ከማግኘት ባሻገር የተለያዩ ልምዶችን ለማካበትም እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡   

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!
ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-
ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA
የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት