አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ከፍተኛ የእንሰት አምራች በሆነው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመጀመሪያውን የእንሰት መፋቂያና ማብላያ የሙከራ ማዕከል /Enset Processing Pilot Plant/ በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ አቋቁመው ታኅሣሥ 12/2016 ዓ/ም በይፋ ሥራ አስጀምረዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የእንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ እንደገለጹት ሥራው ቴክኖሎጂዎቹን ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ አምጥቶ ለማስተዋወቅ በማለም ከቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በቀረበ ጥያቄ መሠረት ከስምንት መቶ ሺህ ብር በላይ በሆነ የገንዘብ ድጋፍ የተሠራ ነው፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ሳይቶች የሚሆኑ የተለያዩ የእንሰት ማቀነባበሪያ ማሽኖችን አምርቶ ለቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በማስረከብ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመጀመሪያውን እንዲሁም እንደ ሀገር 4ኛውን የእንሰት ማቀነባበሪያ የሙከራ ማዕከል ማቋቋም መቻሉን ዶ/ር አዲሱ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶ/ር አዲሱ ዩኒቨርሲቲው ማሽኖችንና የማብላያ ግብዓቶችን ከማቅረቡ ባሻገር ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በማዕከሉ እንዲሠሩ ላዘጋጃቸው ወጣቶች በማሽኖቹ አጠቃቀም፣ ማብላላትና የእርሾ አጠቃቀም ላይ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮና በክልሉ ከሚሠሩ ሌሎች አጋር አካላት ጋር ቴክኖሎጂዎቹን ለማስተዋወቅና ለማስፋፋት የሚያስችሉ ሥራዎችን በትብብር ለመሥራት ፍላጎቶች በመኖራቸው ለዚህ የሚረዱ ምክክሮችም እየተደረጉ ነው፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው የእንሰት ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋት ከተለያዩ አካላት ጋር በትብብር እየሠራ መሆኑን ጠቁመው በቅርቡ በዩኒቨርሲቲው በተደረገው ዓለም አቀፍ የእንሰት ሲምፖዚየም ወቅትም ከተለያዩ የሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሞ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ከቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባባር ተቋቋሞ ሥራ የጀመረው የእንሰት ማቀነባበሪያ ማዕከልም የዚሁ ስምምነት አካል ሲሆን ማዕከሉ ከፍተኛ እንሰት አምራች በሆነው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቦንጋ ላይ መቋቋሙ ቴክኖሎጂዎቹን ከማስተዋወቅና ከማላመድ አንጻር ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንቶች ፎረም ተሳታፊ አመራሮች ማዕከሉን የተመለከቱ መሆኑን የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ በዚህም ከበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች አድናቆትና የአብረን እንሥራ ጥያቄዎች ቀርበዋል ብለዋል፡፡ ይህም አጋጣሚ ቴክኖሎጂዎቹን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና ለማስፋት እንደ ተቋም ለተያዘው ውጥን ተጨማሪ ዕድል ይዞ የመጣ መሆኑን ም/ፕሬዝደንቱ አውስተዋል፡፡ መሰል የትብብር ሥራዎች እንደ ሀገር ቴክኖሎጂዎቹን የመጠቀም ከፍተኛ ፍላጎት ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል ያሉት ም/ፕሬዝደንቱ ይህም በሂደት ቴክኖሎጂዎቹ ወደ ኢንደስትሪ እንዲገቡ ዕድል በመፍጠር ዩኒቨርሲቲውም ሆነ የቴክኖሎጂዎቹ ፈጠራ ባለቤት የሆኑ ግለሰቦች ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ በበኩላቸው አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው እንሰትን እንዲሁም በእንሰት ዙሪያ በዩኒቨርሲቲው የተሠሩና በተግባር ተፈትሸው የተረጋገጡ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅና ለማስፋት ከወልቂጤ፣ ደብረማርቆስና ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋትና ለማስተዋወቅ የሚያግዝና 100 ማሽኖችን አምርቶ እንሰት አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ማዳረስን ዓላማ ያደረገ ስምምነት ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲና ቴክኖሎጂዎቹን ከሚያመርቱ አምስት የግል ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመሥራት በ‹‹USAID›› የሚደገፍ የሦስትዮሽ መግበቢያ ሠነድ ተፈርሞ ወደ ተግባር መገባቱንም ዶ/ር ቶሌራ አክለዋል፡፡ ቦንጋ ላይ የተቋቋመው የእንሰት ማቀነባበሪያ ማዕከል አካባባቢው ከፍተኛ የእንሰት አብቃይ እንደመሆኑ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ቶሌራ ምርምር ላይ ተመሥርተው የተፈጠሩት ቴክኖሎጂዎች የዩኒቨርሲቲውን ስምና ዝና ከማጉላታቸው ባሻገር በሌሎች ዘርፎች አብረውን የሚሠሩ ተባባሪ አካላትን እንድናገኝ በሮችን የከፈቱ ናቸው ብለዋል፡፡

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ፣ ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ከለለው አዲሱ እንደገለጹት ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንሰት በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ እንደመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በትኩረት ምርምር ከሚሠራባቸው መስኮች መካከል ዋነኛው ነው፡፡ በአካባቢው በተለያዩ ምክንያቶች እንሰትን የማምረትና የመጠቀም ሁኔታ እየቀነሰ በመምጣቱ ዩኒቨርሲቲው የተመረጡ የእንሰት ዝርያዎችን የማላመድና ችግኞችን በስፋት በማባዛት ለማኅበረሰቡ የማዳረስ ሥራ እየሠራ ይገኛልም ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ሰፋፊ የእንሰት ማሳዎች ያሉት መሆኑን የገለጹት ም/ፕሬዝደንቱ ከማሳዎቹ የሚገኘውን ምርት እንደ ምርምር ተቋም ዘመናዊ በሆነ መንገድ ማቀነባበርንና ምርቱን ለገበያ ማቅረብን ዓላማ በማድረግ በመስኩ ፈር ቀዳጅ ከሆነው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ዘመናዊ የእንሰት ማቀነባበሪያ የሙከራ ማዕከል ማቋቋም ተችሏል ብለዋል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ሥራው ማኅበረሰቡን ትኩረት ያደረገ ሲሆን በቀጣይ ቴክኖሎጂዎቹን የማስፋፋትና ለማኅበረሰቡ የማስተዋወቅ ሥራ በትኩረት ይሠራል፡፡

ከቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በኤሌትሪካል ኢንስታሌሽን የትምህርት ዘርፍ በደረጃ 4 የተመረቀችውና በማዕከሉ ሥልጠና ወስደው ከሚሠሩ ወጣቶች መካከል አንዷ የሆነችው ወጣት መስከረም መላኩ የማሽኖቹ አጠቃቀም መጀመሪያ አካባቢ ከብዷቸው እንደነበርና በሂደት በአግባቡ መጠቀም እንደጀመሩ ተናግራለች፡፡ ማሽኖቹ ለአጠቃቀም ቀላልና ምቹ እንዲሁም ከባህላዊው አሠራር ጋር ሲተያዩ በእጅጉ ጊዜና ጉልበት የሚቆጥቡ መሆናቸውን የምትናገረው ወጣት መስከረም ቦንጋ ዩኒቨርሲቲም ሆነ ሌሎች አካላት ድጋፍ የሚያደርጉላቸው ከሆነ ከጓደኞቿ ጋር በመደራጀት በዘርፉ የመሥራት ውጥን መያዟን አክላለች፡፡ ተክሉን በዚህ መልክ ማቀነባበር ከተቻለ ጥራት ያለው ምርት ይዞ ወደ ገበያ በመውጣት የተሻለ ገቢ ማግኘት ይቻላል የሚል እምነት እንዳላትም ተናግራለች፡፡

ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንቶች ፎረም ተሳታፊ የሆኑ የትምህርት ሚኒስቴርና የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ማዕከሉን የጎበኙ ሲሆን ቴክኖሎጂዎቹ በተግባር የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱና ከተክሉ የሚገኘውን ምርት እና ጥራት በእጅጉ የሚያሻሽሉ እንዲሁም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠርና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንጻር ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ የተክሉን ምርት የመጨመርና በማይታወቅባቸው አካባቢዎች የማላመድና የማስተዋወቅ  እንዲሁም በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተሠሩ የማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎችን የማስፋፋት ጉዳይ ላይ ዩኒቨርሲቲዎች በመተባበር መሥራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት