አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ሚኒስቴር ሱፐርቪዥን ቡድን ለዩኒቨርሲቲው በሰጠው ግብረ መልስና በሌሎች ተያያዥ ተቋማዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር ከታኅሣሥ 04-11/2016 ዓ/ም በሁሉም ካምፓሶች ከመምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ከዩኒቨርሲቲው መምህራን በኩል ከቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች መካከል ትምህርት ሚኒስቴር የቀረፀው ሥርዓተ ትምህርት መመሪያ አተገባበር፣ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ዝግጅት፣  የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች መግቢያ ፈተና፣ ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝ አስተዳደር ለመሸጋገር እያደረገ ያለው ቅድመ ዝግጅት፣ የዩኒቨርሲቲዎች ልየታ፣ የሴት መምህራን ልዩ ድጋፍ፣ የተማሪዎች ቅበላ ቁጥር ማነስ፣ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ፣ ለምርምር ሥራና ለተግባር ትምህርት የበጀት እጥረት፣ የመምህራን ውል ስምምነት፣ የመማር ማስተማር ግብአት በወቅቱ አለመቅረብ፣ የሬጅስትራር አገልግሎት አሰጣጥ፣ የግንባታዎች ጥራት ችግር፣ በሳውላ ካምፓስ የመማሪያ ክፍሎች እጥረት፣  የመምህራን መዝናኛ ቦታዎች ጥራታቸውን የጠበቁ አለመሆን፣ የመኖሪያ ቤት ችግር፣ የክረምት የትርፍ ሰዓት ክፍያ እና ሌሎችም ርእሰ ጉዳዮች ይጠቀሳሉ፡፡

በሌላ በኩል ከአስተዳደር ሠራተኞች የመዋቅር ማሻሻያ ሥራ ሂደት፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ የተማሪዎች መኝታ፣ መመገቢያ፣ መማሪያና ማንበቢያ ቦታዎችን ምቹና ማራኪ ማድረግ፣ የገቢ ማስገኛ አማራጮችን ማሳደግ፣ የንጽሕና መጠበቂያና የደንብ ልብስ በጊዜ አለመሰጠት፣ የትራንስፖርት ችግር፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲሁም የአመራሩና ሠራተኛው ጤናማ ግንኙነትን አስመልክቶ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡

በውይይቱ ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በሚመለከታቸው አካላት ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት በመስጠት ቤተ ሙከራዎችን ማሳደግ፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብና አስተዳደር ጋር ጤናማ ግንኙነት መፍጠር፣ ውጤታማ የመዋቅር ማሻሻያ ማከናወን፣ የተማሪዎች መኝታ፣ መመገቢያ፣ መማሪያና ማንበቢያ ቦታዎችን ምቹና ማራኪ ማድረግና ሌሎችም ሥራዎችን ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የታቀዱ ሥራዎችን ለማሳካት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚፈልግ በመሆኑ በመግባባትና በትብብር መሥራት እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡

እንደ ሀገር የገጠመን የበጀት ችግር በዩኒቨርሲቲው ሥራዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ የተጠቀሰ ሲሆን አቅም በፈቀደ መልኩ በሳውላ ካምፓስ አንድ መማሪያ ክፍል ለመገንባት፣ የመምህራን መዝናኛ ቦታዎችን ጥራት ለማስጠበቅና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ዕቅድ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት