የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት በ2016 የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲው ለመጡ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች ከታኅሣሥ 04-5/2016 ዓ/ም የሕይወት ክሂሎት ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ እንደገለጹት የሥልጠናው ዓላማ በሥርዓተ ጾታ ምንነት ዙሪያ የሚስተዋሉ የተዛቡ አመለካከቶችን በማስቀረት እንዲሁም ሴት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመፍታት ሕይወታቸውን በተሳካ መንገድ እንዲመሩ እና ዓላቸውን ከግብ እንዲያደርሱ ግንዛቤ ማስጨበጥ ነው፡፡

የሳይኮሎጂ ት/ክፍል መምህር አቶ ማርቆስ ካንኮ በሰጡት ሥልጠና ራስን መውደድ፣ መንከባከብ፣ የእችላለሁ ባይነት መንፈስን ማዳበር፣ ከሌሎች ጋር በሚኖር መስተጋብር መጥፎ ስሜትን ከሚፈጥሩ ቃላት መቆጠብ እንዲሁም የምንፈልገውን ነገር ማወቅና የማይጠቅሙ ነገሮችን ላለማድረግ ጽኑ አቋም በመያዝ እምቢ ባይነትን መለማመድ ለነገው ሕይወት ስኬታማነት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ለራሳችን የሚኖረን አሉታዊ አመለካከት የበታችነትና የአልችልም ባይነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ መሆኑንም አክለዋል፡፡  

ሥልጠናው በጭንቀት መንስኤዎችና ውጤቱ፣ ለራስ የሚሰጥ ክብር፣ የአቻ ግፊትና የሚገጥሙ አሉታዊ ተግዳሮቶች እንዲሁም መሰል ተያያዥ ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት