የእናቶችንና ሕፃናትን ጤና ለማሻሻል በሚተገበረው ‹‹AMU-IUC›› ፕሮጀክት III ሥር ከሚከናወኑ ምርምሮች አንዱ የሆነውንና በጋርዱላ ዞን ዲራሼ ወረዳ በነፍሰጡር እናቶችና ሕፃናት ጤና ሁኔታ ላይ በቪዲዮ የተመሠረተ የጤና ትምህርት የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለማወቅ የተደረገውን የሙከራ ጥናት ውጤት ለማኅበረሰቡ ለማስተዋወቅ ጥር 04/2016 ዓ/ም በጊዶሌ ከተማ ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኅብረተሰብ ጤና ት/ክፍል መምህርና የ‹‹AMU-IUC›› ፕሮጀክት III አስተባባሪ አቶ ዋንዛሁን ጎዳና በፕሮጀክቱ አማካኝነት የ3 ዲግሪ ትምህርታቸውን ቤልጂዬም ሀገር በሚገኘው ኼንት ዩኒቨርሲቲ /Ghent University/ በመከታተል ላይ ሲሆኑ የመመረቂያ ጥናታቸውን ‹‹Effects of video-based health education on health status of pregnant mothers and their infants (from 0 to 6 months) in Dirashe district Southern Ethiopia - A cluster randomized controlled trial›› በሚል ርእስ አከናውነዋል፡፡

ተመራማሪው አቶ ዋንዛሁን እንደገለጹት በአካባቢው የእናቶችና ሕፃናት ጤናን አስመልክቶ አገልግሎቱን በሚሰጡ ባለሙያዎች ብቃትና ቁጥር ማነስ፣ በሥራ ጫናዎችና በሌሎችም ምክንያቶች እናቶችና ሕፃናት የሚገባቸውን አገልግሎትና ድጋፍ እያገኙ አለመሆኑ ለጥናቱ መነሻ ሆኗቸዋል፡፡ በመሆኑም በቪዲዮ የተደገፉ ትምህርቶች ቢሰጡ አገልግሎቱን ለማሻሻል የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ለማየትና ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ሃሳቦችና አሠራሮችን ለመጠቆም ጥናቱ ተሠርቷል፡፡

እንደ ተመራማሪው በዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት(WHO)፣ ‹‹UNICEF- Infant and Young Child Feeding (IYCF) practices Manual››፣ ‹‹WHO-UNICEF key messages booklet on the community››፣ ‹‹IYCF counseling package›› እና በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ተግባራዊ እየሆኑ ባሉት ‹‹Essential Nutrition Action (ENA)›› መመሪያ መሠረት በማድረግ የእናቶችና ሕፃናት ጤና እና አመጋገብ ላይ የተዘጋጁት 10 ቪዲዮዎች በጭውውት፣ በክርክርና በልምድ ማጋራት መልክ ባህሉን በማይጻረር መንገድ በአካባቢው ተወላጆችና ቋንቋ ተሠርተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከስምንት ቀበሌያት የተመረጡ ነፍሰ ጡር እናቶች በየሁለት ሳምንቱ ቪዲዮውን እንዲያዩ ተደርጎ ቪዲዮውን ካላዩ የሌሎች ስምንት ቀበሌያት እናቶች ጋር ያለው ልዩነት ተመዝግቧል፡፡

ነፍሰ ጡር እናቶቹ ከእርግዝናቸው ሦስት ወራት ጀምሮ ጨቅላ ሕፃናቱ ስድስት ወር እስኪሞላቸው ድረስ ክትትልና ምርመራዎች የተደረጉ ሲሆን በአራስ ሕፃናት የጡት ወተት መጠንን በላቦራቶሪ ለመለካት የተመረጡ ናሙናዎች ተወስደዋል፡፡ በጥናቱ ሂደት የጽንስ ክትትል፣ የወባ፣ የደም ማነስና የሰገራ ምርመራዎች፣ የአይረን ፎሌት ንጥረ ነገር አወሳሰድ፣ የሥነ ምግብ፣ የምግብ ዋስትናና አጠቃላይ የጤና ሁኔታ ክትትሎች የተካሄዱ ሲሆን በምርመራ ለተገኙ ወባና ደም ማነስ ወዲያውኑ እንዲሁም ከስድስት ወር ጀምሮ ለተገኙ የአንጀት ጥገኛ ትላትል በመመሪያው መሠረት ሕክምና እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡

እንደ ተመራማሪው የእናቶችን ግንዛቤ ማሳደግ ባላቸው አቅም አመጋገባቸውን በማስተካከል፣ ንጽሕናቸውን በመጠበቅና ተገቢውን የሕክምና ክትትል በማድረግ ጤናማ የእርግዝናና የወሊድ ጊዜ እንዲኖራቸው እንዲሁም ጤናማና ክብደቱ የተስተካከለ ልጅ ለመውለድ የሚያስላቸው ሲሆን ደም ማነስን በመቀነስ ውርጃ እንዳያጋጥምም ይረዳል፡፡ የእናቶችን ግንዛቤ ለማሳደግ የተጠቀሙበት በቪዲዮ የተመሠረተ የጤና ትምህርት እናቶች በየቀኑ የአይረን ፎሌት ንጥረ ነገር እንዲወስዱና የደም ማነስ እንዲቀንስ፣ አመጋገባቸው እንዲሻሻል፣ በጤና ተቋም እንዲወልዱ፣ ክብደታቸው የተስተካከለ ልጆችን እንዲወልዱ፣ ልጃቸውን እስከ ስድስት ወር የእናት ጡት ብቻ እንዲመግቡና በአራስ ሕፃናት ውስጥ የጡት ወተት መጠን እንዲሻሻል አስተዋጽኦ ማድረጉን የጥናቱ ውጤት አሳይቷል፡፡

ተመራማሪው በጥናታቸው ሂደት ለእናቶች በተደረጉ ምርመራዎች አንዳንድ ያልተጠበቁ ውጤቶችን ማግኘታቸውን የጠቀሱ ሲሆን ለአብነትም ከተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች አንዱ የሆነውና በአካባቢው ስለመገኘቱ እምብዛም የማይገመተው ሺሽቶሶሚያሲስ/ቢልሃርዚያ/ በተለይም ወንዞች ባሉባቸው አካባቢዎች በከፍተኛ ሁኔታ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም ለጨቅላ ሕፃናት ከጡት ወተት ውጪ በመመገብ ምክንያት በአንድ ወራቸው ጃርዲያ ያለባቸው ጨቅላ ሕፃናትን ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህ ግኝት በአካባቢው የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎችን አስመልክቶ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለውን ጨቅላ ሕፃናት በላቦራቶሪ እንዲመረመሩ የማይፈቅድ መመሪያ መፈተሽ እንዳለበት ጥቆማ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡

የእርሳቸውን ጥናት ጨምሮ በሌሎች የፕሮጀክቱ ጥናት ውጤቶች ላይ በመመርኮዝ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ የሚፈጥሩ መልእክቶችን በአማርኛ፣ ጋሞኛና ዲራሽኛ ቋንቋዎች ለማስተላለፍ ከደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ጋር ስምምነት መፈጠሩንና የአየር ሰዓት ግዢ መፈጸሙን ተመራማሪው ጠቁመዋል፡፡ አቶ ዋንዛሁን ምርምሩን በገንዘብና በሌሎች መንገዶች ለደገፉት ‹‹VLIR-OUS››፣ ‹‹AMU-IUC››፣ ‹‹Ghnet University Global Minds Fund›› እና ‹‹Capacity building Fund››፣ ‹‹Department of Diagnostic Sciences›› እንዲሁም መረጃ በመሰብሰብም ሆነ ሌሎች ተልእኮዎች በምርምሩ የተሳተፉ ባለሙያዎችን ሁሉ አመስግነዋል፡፡

በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል በሙያቸው ሚድዋይፍ የሆኑት ሲስተር አስረሳሽ ወንድሙ የጥናቱ ሂደት አድካሚ እንደነበር አስታውሰው በጥናቱ የተካተቱ እናቶች ቀስ በቀስ ግንዛቤያቸው እያደገ ሲመጣና ጥናቱ እነርሱን ለማገዝ የሚጠቅም መሆኑን ሲረዱ በሙሉ ፈቃደኝነት ክትትልና ምርመራውን ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ጥናቱ የእናቶችና ጨቅላ ሕፃናት ጤናና ሥነ ምግብን አስመልክቶ ዕውቀት የጨበጥኩበት ነው ያሉት ሲስተር አስረሳሽ የጥናት ውጤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ደርሶ በአካባቢው ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

የጋርዱላ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ኩናሎ ጥናቱ የጤናውን ዘርፍ ለመደገፍና ለሚታዩ ችግሮች መፍትሔ ለመፈለግ የሚረዳ በመሆኑ በአካባቢው መከናወኑ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል፡፡ በጥናት ውጤቱ ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆንና የእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲጠበቅ የዞኑ አስተዳደር የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቱ ኩምሳ በበኩላቸው የጤና ሥራ የአንድ ወቅት ሥራ ሳይሆን በየጊዜው አዳዲስ ጥናቶችን በማድረግ ለሚገኙ በሽታዎች የሕክምና አሰጣጥ ዘዴዎችና የመከላከል ተግባራት ላይ የሚሠራበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ሀገር አሁን ባለንበት ሁኔታ ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንዲሁም በጠፉና እንደ አዲስ በሚከሰቱ በሽታዎች ጫና ውስጥ ነው ያለነው ያሉት ኃላፊው መሰል ጥናታዊ ጽሑፎች የጤና ሥርዓቱን ለመደገፍ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ መጨረሻ ለጥናቱ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የምስጋና ምስክር ወረቀትና ሽልማት ተበርክቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት