8ው ዙር የማኅበረሰብ ጉድኝት ቀን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በደማቅ ሁኔታ ጥር 6/2016 ዓ/ም ተከብሮ ውሏል፡፡ በዕለቱም ዩኒቨርሲቲው በአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢው የሚገኙ የተፈጥሮና የቱሪስት መስህብ ጸጋዎችን የሚያንጸባርቅ፣ ለከተማው ውበት ከፍ ያለ አበርክቶ ያለውና በ17.2 ሚሊየን ብር በከተማው መግቢያ ላይ ያስገነባውን አደባባይ ያስመረቀ ሲሆን የከተማው ማዘጋጃ ቤትና ማኅበረሰቡ አደባባዩ በጥንቃቄ እንዲያዝ በጋራ እንዲሠሩ ማሳሳቢያ ተሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ዩኒቨርሲቲው በየትምህርት መስኩ ሳይንሳዊ ዕውቀትን መሠረት በማድረግ እንዲሁም በማኅበረሰብ ጉድኝት ተልእኮ ዘርፍ ሀገራዊና አካባቢያዊ የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራዎችን እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የሚሠራቸውን ተግባራት አስመልክቶ በቂ መረጃና ግንዛቤ ካለመያዝ የተነሳ ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ተልእኮውን በአግባቡ እንዳልተወጣ በአንዳንድ አካላት የትችት አስተያየቶች ይቀርባሉ ያሉት ፕሬዝደንቱ ከሚታዩ ግዙፍ ቁሳዊ ሥራዎች ባሻገር ከዕውቀትና አቅም ግንባታ ጋር የተያያዙ የጤና፣ የሕግና ሌሎች አገልግሎቶችና ሥልጠናዎችን ከግምት ማስገባት እንደሚገባ ፕሬዝደንቱ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋነኛ ትኩረታቸው ዕውቀትና ቴክኖሎጂን በማመንጨት ማላመድና ኅብረተሰቡም ሆነ መንግሥት አስፋፍቶ እንዲጠቀምባቸው መንገድ መክፈት ነው ያሉት ፕሬዝደንቱ በዚህ ረገድ የእንሰት ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች ለአብነት የሚጠቀሱ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው የእንሰት አመራረትን የሚያሻሽሉ በምርምር የተገኙ ፈጠራዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በማዘጋጀት ሥልጠናዎችን እየሰጠና የማስተዋወቅ ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎቹን ለማኅበረሰቡ በማዳረስ ረገድ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ትኩረት ሊሰጡበት እንደሚገባ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ተልእኮዎቹን በአግባቡ እንዲወጣ የአካባቢው አስተዳደርና የማኅበረሰቡ ድጋፍና አጋርነት ሁሌም እንደሚያስፈልገው ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡     

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተባባሪ ፕሮፌሰር በኃይሉ መርደኪዮስ እንደገለጹት በዚህ የማኅበረሰብ ቀን ላይ የሚታዩና የሚነገሩ ሥራዎች ሁሉ በምርምር የዳበሩና በማኅበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ ከግብ የደረሱ፣ እፎይታንና ጤናማ ሕይወትን ለመምራት የሚረዱ፣ የማኅበረሰብ ተሳትፎ የተረጋገጠባቸው እንዲሁም ወደ ማኅበረሰቡ ዘንድ ወርደው ውጤታማ የሆኑ ሥራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ቀንን የዓመታዊ ሥራ ማስተዋወቂያ፣ ስኬቶችን ማሳያና ማጉያ እንዲሁም ለወደ ፊት ጉድኝት የማኅበረሰብን ሃሳብ ማሰባሰቢያ መድረክ አድርጎ የሚጠቀም ሲሆን ጠቃሚ የሆኑ ሃሳቦችን ከማኅበረሰቡ በመውሰድ የአሠራር ስልቶችን ለማስተካከል የማኅበረሰቡ ፍላጎት የሚደመጥበትና እኛም እንደ ዩኒቨርሲቲ ያሉብንን ተግዳሮቶች ለማኅበረሰቡ የምናስረዳበት መድረክ ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በ2015 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው የተከናወኑ አበይት የማኅበረሰብ ጉድኝት ክንውኖችን የተመለከተ ሪፖርት ሲያቀርቡ ዩኒቨርሲቲው የጋሞ ባይራ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ ክፍሎች፣ የተማሪ ማደሪያዎች (ዶርሚተሪዎች)፣ ላቦራቶሪዎች፣ አይ ሲ ቲ፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የመመገቢያ አዳራሾችና ቢሮዎችን በግብዓት ለማደራጀት 31 ሚሊየን ብር፣ በከተማው መግቢያ የሚገኘውን አደባባይ ግንባታ ለማከናወን 17.2 ሚሊየን፣ የሻማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ለማስፈጸም 1.9 ሚሊየን ብር እና  በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ተጀምሮ የነበረውን የቆላ ሻራ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ 3.69 ሚሊየን ብር በጀት መድቦ ፕሮጀክቶቹ ተከናውነው ለማኅበረሰቡ ተደራሽ መሆናቸውን እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃና ልማት ሥራዎች 3.6 ሚሊየን ብር እና የነጻ ሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሥራዎችም 3.2 ሚሊየን ብር በጀት ትኩረት ተሰጥቷቸው ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ተጠቃሾች መሆናቸውን ዶ/ር ተክሉ አሳውቀዋል፡፡

ዶ/ር ተክሉ አክለውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበጀት ዕጥረት፣ ያልተቀናጁና የተበጣጠሱ የድጋፍ ጥያቄዎች ከተቋማት መቅረብ፣ ለዩኒቨርሲቲው የተተው ሥራዎችን አለመለየትና የተቋማትን ዕቅድ በጥሬው የማቅረብና የማኅበረሰብ ጉድኝት ሥራ የገንዘብና የግብዓት ድጋፍ መስጠት ብቻ አድርጎ የመውሰድ ግንዛቤ ችግር ካጋጠሙ ተግዳሮቶች መካካል ናቸው ብለዋል፡፡

በዕለቱ በዩኒቨርሲቲው ለሁለት ዓመታት ሲማሩ የነበሩ 390 የተቀናጀ ተግባር ተኮር ትምህርት ያጠናቀቁ ጎልማሶች የተመረቁ ሲሆን ከነዚህም መካካል 228ቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ለስምንት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሁለት ሁለት በድምሩ 16 ዘመናዊ ማይክሮስኮፖች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ከዩኒቨርሲቲው ውጪ ለምዕራብ ዓባያ ወረዳ፣ ለ“STEM Power” እና ለተባባሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን (UNCHR)፣ ከዩኒቨርሲቲው ለስድስት የትምህርት ክፍሎችና ፋከልቲዎች የምሥክር ወረቀት እንዲሁም ለማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እና ለሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ መኩሪያ ልዩ የዕውቅና ሽልማትና የምሥክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ የጋሞ ዞን ም/ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ፣ የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ፣ የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ ደረጀ ጳውሎስ እና የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማና የቀበሌ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮችና አስተባባሪዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት