አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአርባ ምጭ ከተማ መግቢያ ላይ በ17.2 ሚሊየን ብር ያስገነባውን አደባባይ ጥር 6/2016 ዓ/ም በማስመረቅ ለአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር አስረክቧል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ምክትል ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው ጥራት ያለው ትምህርትና የምርምር ሥራዎችን ከማከናወኑ ባሻገር በኅብረተሰብ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመለየት ችግር ፈቺ የሆኑ ሥራዎችን እንደሚያከናውን ጠቁመው በዋናነትም የከተማውን ጽዳት በመጠበቅና ወደ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በመቀየር ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ለአካባቢው ሙዝ አብቃይ አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማሰራጨት እና የትስስር ኢኮኖሚን የማሳደግና መሰል ሥራዎችን ሲተገብር መቆየቱን ም/ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ አደባባዩ የቱሪስት መስህብ የሆነችውን ውቢቷን አርባ ምንጭ ከተማንና አካባቢዋን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይና የከተማው ማዕከል ላይ የተገነባ መሆኑን ገልጸው የአካባቢው ማኅበረሰብና የከተማው አስተዳደር በልዩ ሁኔታ እንዲንከባከበውና እንዲጠብቀው አሳስበዋል፡፡ በቀጣይም መሰል ሥራዎችን ዩኒቨርሲቲው አጠናክሮ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝደንት ወ/ሮ ታሪኳ ወ/መድኅን በዩኒቨርሲቲው የተገነባውን የአደባባይ ግንባታ ሥራ ረቂቅ ዲዛይን በተመለከተ አጭር ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ግንባታው ከተማውና አካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ገጽታ እንዲያንጸባርቅ  ታሳቢ ተደርጎ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡
ወ/ሮ ታሪኳ በሰጡት የግንባታው ረቂቅ ዲዛይን ትንታኔ የንድፍ ጽንሰ-ሃሳቡ የተመሠረተው ፊትና ጀርባ የቆሙ ሁለት ቋሚ ዘንጎችን ባሰረው ክብ ቀለበት ላይ ሲሆን እነዚህ ሁለት ዘንጎች ሁለት የሙዝ ወይም የእንሰት ቅጠሎችን፣ የዓባያና ጫሞ ሐይቆችን እንዲሁም የሴቻና ሲቀላ የከተማው ክፍሎችን በመወከል የአካባቢውን የተፈጥሮ ፀጋዎች ረቂቅ በሆነ መልኩ የሚያሳዩ መሆኑን እንዲሁም አቃፊው ክብ ደግሞ ሁለቱንም መዋቅሮች አቅፎ በመያዝ ሁለንተናዊነትና አንድነት እንዲገልጽ ተደርጓል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በመጀመሪያው ቅጠል የሞዛይክ አርት ላይ በሐይቆቹ የሚኖሩ እንስሳትን እንዲሁም የሁለተኛው ቅጠል ሞዛይክ አርት ደግሞ የዓባያና ጫሞ ሐይቆች እና የነጭ ሳር ፓርክ የመሬት አቀማመጥ/Landscape/ እንደሚያሳይ ወ/ሮ ታሪኳ ገልጸዋል፡፡ ከሁለቱ ዘንጎች ስር ያለው ውኃ አርባ ምንጭን እና ተንሳፋፊው ቁጥሩ 40 መሆኑ አርባ ምንጮችን ይወክላል ሲሉ ም/ፕሬዝደንቷ ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን በመግለጽ አሁን ላይ ገንብቶ ለከተማ አስተዳደሩ ያስረከበው አደባባይ የከተማውን ውበት የሚያጎላ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም የከተማውን አጠቃላይ ገጽታ የሚቀይርና ሌሎችም ወደ ልማት ሥራ እንዲገቡ የሚያነሳሳ ትልቅ ሥራ መሆኑን ጠቁመው ኅብረተሰቡም ይህንንና መሰል መሠረተ ልማቶችን እንደራሱ ንብረት እንዲጠብቅ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የጋሞ ዞን ም/ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ እንደገለጹት የዞኑን ገጽታ በሚያሳይ መልኩ የተገነባው አደባባይ አካባቢው ምን ያህል በተፈጥሮ የተዋበ እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም ዞኑ ዩኒቨርሲቲው በሚያከናውናቸው ሥራዎች ሁሉ ከጎኑ እንደሚሆን አስተዳዳሪው ገልጸው ዩኒቨርሲቲውም ላበረከተው አስተዋጽኦ አመሥግነዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው አደባባዩ ከተማው ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ምቹ እንዲሆን እየተከናወኑ ካሉ በርካታ የፕሮጀክት ሥራዎች  መካከል አንዱ ሲሆን ከተማውን ትኩረት በማድረግ በልዩ ሁኔታ የተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በከተማው ውስጥ በርካታ አደባባዮች ቢኖሩም የአሁኑን አደባባይ ልዩ የሚያደርገው ወደ ከተማው ሲገባ ፊት ፊት የሚገኝ መሆኑ፣ በአካባቢው  ክረምትና በጋ የሚፈስ የኩልፎ ወንዝ በመኖሩ የመልማት አቅሙ ከፍተኛ ስለሆነ እንዲሁም በአቅራቢያው ትልቅ የሕዝብ መሰብሰቢያ ስቴዲየም መኖሩ እና የከተማው መነሻም በመሆኑ ለሁሉም አቅም ሊሆን የሚችል ነው ብለዋል፡፡

የግንባታ ሂደቱ ብዙ ውጣ ውረድ የነበረው ቢሆንም የከተማውንና የዩኒቨርሲቲውን የአብሮነት ቆይታ ሊያሳይ በሚችል መልኩ እንዲጠናቀቅ ሆኖ ለከተማው መበርከቱን ያመላከቱት ዶ/ር ተክሉ በቀጣይ የከተማ አስተዳደር ኃላፊነቱን በመውሰድ የመብራትና ውኃ ስርጭት እንዳይቋረጥ አስፈላጊውን ሁሉ የማድረግ እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በባለቤትነት ይህንን ሀብት በመጠበቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የጋሞ ዞን፣ የአርባ ምንጭ ከተማና የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው መካከለኛ  ኃላፊዎች፣ መምህራንና ሠራተኞች እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ ተገኝተዋል፡፡

 አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት