የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ "Jhpiego" ጃፓይጎ ከተሰኘ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር በኮሌጁ በ“e-learning” የአካዳሚክ ሥራዎችን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር በሚያስችል የኦንላይን መተግበሪያ ፕላትፎርም አጠቃቀምና አተገባበር ላይ ልምድ ለማካፈል የተዘጋጀ የአንድ ቀን ወርክሾፕ ጥር 3/2016 ዓ/ም አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ልዩ ረዳት ዶ/ር ነጂብ መሐመድ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት አሁን ባለንበት 21ው ክፍለ ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ በአብዛኛው ከተለመደው አሠራር ተቀይሮ ወደ ዲጂታል አሠራር እየገባ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የዩኒቨርሲቲው ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ“e-learning” ፕላትፎርምንና ሌሎች የኦንላይን አሠራሮችን በመጠቀም የመማር ማስተማሩን ሥራ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ የጀመራቸው ሥራዎች እንደ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁን በመስኩ ፈር ቀዳጅ የሚያደርገውና ከጊዜው ጋር አብሮ የሚሄድ ተግባር መሆኑን አውስተዋል፡፡ የ“e-learning” ፕላትፎርም በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች ያለ ፕላትፎርም መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ነጂብ በመሆኑም ሌሎች ካምፓሶችም ከሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ልምድ በመውሰድ ወደ እዚሁ አሠራር መግባት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ በበኩላቸው ወርክሾፑ በዋናነት በኮሌጁ በ“e-learning” የአካዳሚክ ሥራዎችን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር ተግባራዊ እየተደረጉ በሚገኙ ፕላትፎርሞች አጠቃቀምና አተገባበር ዙሪያ እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎችን ለማስተዋወቅና በሃሳብ ለማዳበር እንዲሁም ልምድ በማካፈል ተሞክረው ወደ ሌሎች ካምፓሶች እንዲሰፋ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ በኮሌጁ ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙ እነዚህ አሠራሮች የትምህርት ጥራትን እንዲሁም ብቃት ያላቸውና ተወዳዳሪ የሕክምናና ጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት በእጅጉ የሚያግዙ መሆናቸውን የገለጹት ዶ/ር ደስታ እንደ ኮሌጅ የትምህርት አሠጣጡን ከተለመደው አሠራር ለማውጣትና በዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የታገዘ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጃፓይጎ "Health Workforce Improvement Program" የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ ፕሮግራም የአቅም ግንባታና ትምህርት ዘርፍ አማካሪ አቶ ጌታነህ ግርማ ድርጅቱ የጤና ባለሙያዎች ትምህርት ላይ እያሉ ተገቢውን ክሂሎትና አመላካከት አግኝተው እንዲወጡ የሚያስችሉና በዘርፉ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የሚያግዙ  ሥራዎች ላይ በማተኮር እየሠራ ነው፡፡ ድርጅቱ በየተቋማቱ የሚገኙ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ጽ/ቤቶችን ማጠናከር፣ ለመምህራን የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠት፣ የተግባር ትምህርትን ማጠናከር፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስታንዳርዶችን ማዘጋጀትና በእነዚሁ ስታንዳርዶች መሠረት ተቋማት ራሳቸውን እንዲገመግሙና ማሻሻያዎች እንዲያደርጉ ማድረግ ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑንም አውስተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ድርጀቱ በትብብር ከሚሠራባቸው ተቋማት መካካል አንዱ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጌታነህ በኮሌጁም የትምህርት ጥራትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በኮሌጁ የመልቲ ሚዲያ ስቱዲዩ እንዲቋቋምና ኮርሶች በቪዲዮና በድምጽ ታግዘው እየተዘጋጁ መሆኑ፣ የ“E-learning” ፕላትፎርምን በመጠቀም ፈተናዎች በኮምፒውተር ብቻ ታግዘው እየተሰጡ መሆናቸው፣ የሥርዓተ-ትምህርቶች አተገባበርን መከታተል የሚያስችል ዳሽቦርድ ተዘጋጀቶ ሙከራ ላይ መሆኑ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የኮሌጁ ተቋማዊ ጥራት ማጎልበቻ ማ/ጽ/ቤት አስተባባሪና ትኩረት የሚሹ ቆላማ አከባቢ በሽታዎች የምርምር እና ሥልጠና ማዕከል ዳይሬክተር ረ/ፕ አብነት ገ/ሚካኤል የኮሌጁን ተሞክሮ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት ኮሌጁ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን የ“e-learning” ፕላትፎርምን በመጠቀም የመማር ማስተማሩንና የፈተና ሥርዓቱን ወደ ዲጂታል ለመቀየር እየሠራ ያለው ሥራ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ አግባብ ከ2016 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በኮሌጁ ፈተናዎች በፕላትፎርሙ በመጠቀም እየተሰጡ መሆናቸውን የገለጹት አስተባባሪው ኮምፒውተር ላይ የተመሠረተ ፈተና የፈተና አስተዳደርን በቅልጥፍና በማከናወን፣ ፈተናዎች በእጅ ሲታረሙ ሊፈጠሩ የሚችሉ  ስህተቶችን  በማስወገድ፣  ተማሪዎች ፈተናውን ካጠናቀቁ በኋላ ወዲያውኑ አፈፃፀማቸውን እንዲያውቁት ለማድረግ፣ በፈተና ኅትመትና ማባዛት ሲባል የሚወጡ ከፍተኛ ወጪዎችን ከማስቀረት አንፃር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ረ/ፕ አብነት በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ተማሪዎች ውጤታማና ብቁ የሚሆኑት  በሚማሩበት ፕሮግራም ያለው ሥርዓተ-ትምህርት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲደረግ ሲሆን ከዚህ አንፃር ኮሌጁ ሥርዓተ-ትምህርቶች በአግባቡ መተግበራቸውን ለመቆጣጠር የሚያስችል "Curriculum Implementation Monitoring Dashboard" የተሰኘ ፕላትፎርም በማበልጸግ  በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ፕላትፎርሙ በኦንላይን የሚሠራ ሲሆን በሥርዓተ-ትምህርቶቹ ውስጥ የተካተቱ ተግባራትና ስታንዳርዶች መተግበራቸውን ከተማሪዎች በኦንላይን በሚሞላ ፎርም መሠረት መቆጣጠር የሚያስችልና የታዩ ድክመቶች ላይ በአፈጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የሚያግዝ እንደሆነም  ጠቁመዋል፡፡

ከወርክሾፑ ተሳታፊዎች መካከል የሳውላ ካምፓስ አስተዳደር ጉዳዮች ዳይሬክተርና የማርኬቲንግ መምህር አቶ  ዘለቀ ዶሳ በሰጡት አስተያየት በወረክሾፑ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ“e-learning” ፕላትፎርምን ከወሬ ባሻገር በተግባር የቀየረ መሆኑን መረዳታቸውን በዚህም በእጅጉ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ዘለቀ አክለውም ይህንን ፕላትፎርም መጠቀም የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ባሻገር ለአብነት እንደ ሳውላ ካምፓስም ሆነ በሌሎች ካምፓሶች በየጊዜው ለፈተና ኅትመት የሚወጣን ከፍተኛ ወጪ የሚያስቀር በመሆኑ በቀጣይ የኮሌጁ ልምድ ወደ ሁሉም ካምፓሶች እንዲስፋፋና ተግባራዊ እንዲሆን በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት