ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዓባያ ካምፓስ የ2016 ዓ/ም 1ኛ ዓመት ሴት ተማሪዎች የእንኳን ደኅና መጣችሁ አቀባበልና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ነባር ሴት ተማሪዎች የሽልማት አሰጣጥ መርሃ ግብር ጥር 08/2016 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡
ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ እንደ ሀገር በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ሴት ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰው ተማሪዎቹ ውጤታማ ሆነው ትምህርታቸውን በስኬት እንዲያጠናቅቁ መሰል ፕሮግራሞች፣ የሕይወት ክሂሎት ሥልጠና፣ ነባር ውጤታማ ተማሪዎችን መሸለምና ሌሎችም  የትምህርት ተነሳሽነትን የሚጨምሩ መርሃ ግብሮችን እንደሚያዘጋጁ ተናግረዋል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ በበኩላቸው ሴት ተማሪዎች ከወንዶች እኩል ጠንክረው በመሥራት በትምህርትና በማኅበራዊ ግንኙነት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ፕሮግራሙ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በተለይ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች የኢኮኖሚ ችግሮች፣ ጾታዊ ትንኮሳዎችና ሌሎችም መሰል ችግሮች ሲገጥማቸው ለዚሁ ዓላማ በተቋቋመው ቢሮ አማካኝነት ድጋፍ እንደሚያገኙም ዲኑ ጠቁመዋል፡፡

የኮሌጁ  ሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ማስተባባሪያ ጽ/ቤት ባለሙያ ወ/ሮ አበራሽ በቀለ በበኩላቸው ጽ/ቤቱ ሴቶች ከወንዶች እኩል ተፎካካሪ ሆነው ጥሩ ውጤት ማምጣት እንዲችሉ ከመደበኛው ትምህርታቸው ጎን ለጎን በየትምህርት መስካቸው በራሳቸው የትምህርት ዓይነት ፍላጎት በማጠናከሪያ ትምህርት እንዲደገፉ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ለአካል ጉዳተኞች፣ ወላጅ ላጡ፣ የጤና ችግር ላለባቸውና የኢኮኖሚ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በዩኒቨርሲቲው በኩል ድጋፍ እንደሚደረግም ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ባለሙያዋ ጽ/ቤቱ ሴት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ጾታዊ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ከመከታተል ባሻገር ተከስቶ ሲገኝ ማስረጃ በማጠናቀር እርምጃ ያስወስዳል፡፡

በመርሃ ግብሩ በ2015 የትምህርት ዘመን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ የኮሌጁ ሴት ተማሪዎች ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ከእነዚህ መካከል ተማሪ ማርታ ዳንኤል ከጂኦሎጂ ት/ክፍል 3.96፣ ተማሪ መታሰቢያ መስፍን ከፎረንሲክ ኬሚስትሪ ት/ክፍል 3.93 ተማሪ ቤተልሔም ደመቀ ከስፖርት ሳይንስ ት/ክፍል 3.80፣ ተማሪ አናን ወርቅነህ ከባዮሎጂ ት/ክፍል 3.80 እና ተማሪ ያስሚን ሙሐመድ ከባዮቴክኖሎጂ ት/ክፍል 3.77 ያስመዘገቡ ተሸላሚዎች ናቸው፡፡

ተሸላሚ ተማሪ መታሰቢያ መስፍን በመሸለሟ በጣም ደስተኛ መሆኗንና ሽልማቱ ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ መሆኑን ገልጻ አዲስ ገቢ ሴት ተማሪዎች ጠንክረው ከተማሩ ተሸላሚ መሆን ለሁሉም እንደሚቻል መክራለች፡፡

በመርሃ ግብሩ አርአያ የሆኑ ሴት ተማሪዎች የጊዜ አጠቃቀም፣ የጓደኛ አመራረጥና የአጠናን ስልት ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት