የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ከጋሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር ከአርባ ምንጭ ከተማና ከዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ለመጡ ወጣቶች እና ለስፖርት ጽ/ቤት ባለሙያዎች በሰብእና ግንባታ (Mindset) ዙሪያ ከጥር 06-09/2016 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ሕይወት ምንድን ነው? እኔ ማን ነኝ? ለምን ተፈጠርኩ? ያለኝን አቅም የመጠቀም ምን ያህል ብቃት አለኝ? ራእዬን እንዴት እውን አደርጋለሁ? የሚሉ ጥያቄያዊ ርእሰ ጉዳዮች ሥልጠናው ያተኮረባቸው ነጥቦች ሲሆን በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ የሚከሰቱ በጎ ለውጦችን በምን መልኩ ማስቀጠል እንደሚቻል እንዲሁም ትውልዱ በአመለካከቱና በአስተሳሰቡ ላይ የሚያመጣቸው በጎ ተጽዕኖዎችም ተዳስሰዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች በየዘርፋቸው ከሚሰጠው የመማር ማስተማር ተግባር ጎን ለጎን ሰብእናው የተሟላ፣ በዕውቀት የተካነና የተስተካከለ የአእምሮ ውቅር ያለው ዜጋ ማፍራት ከያዛቸው ራዕዮች መካከል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ም/ፕሬዝደንቱ ወጣቶች ላይ የሚሠሩ መሰል የሰብእና ግንባታ ሥልጠናዎችን በቀጣይነት ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ መምህራንና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች እንዲሁም ለሌሎች መሥሪያ ቤቶችም አጠናክሮ ማዳረስ ይገባል፡፡

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና አሠልጣኝ አቶ መርክነህ መኩሪያ የትውልድ ሰብእና ግንባታ ላይ የሚያተኩረው ሥልጠና ለተፈጠረበት ዓላማና ለሚያገለግለው ሕዝብ ታማኝ የሚሆን እንዲሁም በውስጡ ያለውን አቅም አውጥቶ መጠቀም የሚችል ዜጋን ማፍራት እንዲቻል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሠልጣኙ በመልካም ሰብእና የተቀረጸ ትውልድ በፈጠራ ተግባር ላይ በመሳተፍ ራሱንና ሀገርን የመቀየር፣ ኃላፊነትን የመረከብና ሀገርን የማቅናት አቅም አለውም ብለዋል፡፡

የጋሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የወጣት ዘርፍ ም/ኃላፊ አቶ አብዲ መሐመድ ወጣቶቹ ያገኙት ሥልጠና ሰብእናቸውን በመገንባት በቀጣይነት በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲገኙ እንደሚያስችላቸው ገልጸው ሠልጣኞቹ ያገኙትን ክሂሎት በተረዱት መጠን በተግባር ላይ ማዋል እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

ከአርባ ምንጭ ከተማ የመጣው ሠልጣኝ ወጣት ፀጋዬ ተፈራ ሥልጠናው ሰብእናን እንዴት መገንባትና ራስን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል የሚያሳይ መሆኑን ገልጾ ትውልዱ በቀጣይነት ቢያገኘው የተሻለ ማኅበረሰብና ሰብእናው የተሟላ ወጣት መፍጠር እንደሚቻል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ሥልጠናውን ለተከታተሉ ወጣቶች የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን ሠልጣኞች በዩኒቨርሲቲው የሚገኘውን የአእምሮ ማጎልበትና ተግባቦት ማዕከል/Intelligence Enhancement and Dynamic Communication Center (IEDC) ጎብኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት