የዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ ልማት እና ማበልጸጊያ ማዕከል ከኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት/ Entrepreneurship Development Institute (EDI) ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጋር በመተባበር ከጥር 13-18/2016 ዓ/ም ለዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን የኢንተርፕርነርሽፕ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ሥልጠናው በኢንተርፕርነርሽፕ ምንነት፣ የቢዝነስ ፕላን አዘገጃጀት፣ የስኬታማ ኢንተርፕርነሮች ባህርያት እና መሰል ርእሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ "ሥልጠናው ዐይን ከተከፈተ ከሁሉም ነገር ሥራ መፍጠር የሚቻል መሆኑን ያመላከተ ነው" ብለዋል፡፡ አያይዘውም ሥልጠናው ለግልና ለሀገር የሚጠቅም በመሆኑ ለሌሎች አካላት በመስጠት የሥራ ፈጣሪነት አቅማቸውን ለማጎልበት ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡

የሥራ ፈጠራ ልማት እና ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ጀረኔ እንደገለጹት ሥልጠናው ሴት መምህራንን ውስጣዊ የሥራ ፈጣሪነት ችሎታ ግልጽና ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ መመዘን የሚያስችላቸውን መልካም አጋጣሚዎች መለየት፣ አበረታች ግቦችን ማስቀመጥ፣ ግላዊ አቅምን ማሳግ እንዲሁም ሊገጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን በመገምገም እርምጃ መውሰድ በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ የአስተሳሰብ ለውጥ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ የኢንተርፕርነርሽፕ አማካሪና አሠልጣኝ አቶ ፍሬው ዘውዴ ስኬታማ ኢንተርፕርነሮች ለስኬታቸውና ለውድቀታቸው ኃላፊነትን ሲወስዱ በአንጻሩ ስኬታማ ያልሆኑ ኢንተርፕርነሮች በዕድላቸው የሚማረሩና ለውድቀታቸው የተለያዩ ምክንያቶችን የሚደረድሩ ናቸው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ስኬታማ ያልሆኑ ኢንተርፕርነሮች ሁልጊዜ ችግር ብቻ የሚታያቸው፣ አካባቢያቸው ምቹ እንዳልሆነ የሚገልጹ እንዲሁም ብዥታ ውስጥ የሚገቡ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ስኬታማ የሆኑ ኢንተርፕርነሮች ለሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች መፍትሔ የሚያመላክቱ፣ ምቹ አካባቢ የሚፈጥሩ እንዲሁም ዓላማ የሚያስቀምጡ መሆኑን አሠልጣኙ አብራርተዋል፡፡

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ አማካሪና አሠልጣኝ አቶ ስንታየሁ ሽብሩ በበኩላቸው ስኬታማ ኢንተርፕርነር ለመሆን ምን መሥራት እንደሚጠበቅ፣ እንዴት መሥራት እንደሚቻል እንዲሁም ስልታዊ እቅድ ማቀድና መገምገምን አስመልክቶ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡

ስኬታማ ኢንተርፕርነር ለመሆን መልካም አጋጣሚዎችን መጠቀም፣ በመረጃ ልውውጥ ማመን፣ ለስኬትና ውድቀት ኃላፊነት መውሰድ እንዲሁም ስልታዊ እቅድና ዓላማ ማስቀመጥ አስፈላጊ መሆኑ በሥልጠናው ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም በምርት ወይም አገልግሎት ዙሪያ ገለጻ መስጠት፣ ቢዝነሱ የሚከናወንበትን አድራሻ መግለጽ፣ የገበያ ጥናት ማካሄድ እንዲሁም ፋይናንሳዊ ክዋኔዎችን አስመልክቶ ትንታኔ መስጠት ውጤታማ የቢዝነስ ፕላን ለማዘጋጀት ከሚያግዙ ስልቶች ጥቂቶቹ እንደሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ሠልጣኞች በነበራቸው ተግባር ተኮር የስድስት ቀናት የሥልጠና ቆይታ የቢዝነስ ትግበራ ሙከራ እያደረጉ የቆዩ ሲሆን የተሻለ አፈፃፀም መማሳየት ሠልጣኝ መ/ርት ፍቅርተ ሥዩም ማበረታቻ ሽልማት ወስደዋል፡፡ ተግባር ተኮር የቢዝነስ ፕላን በማዘጋጀት ደግሞ መ/ርት እናንዮ ገደበው በተመሳሳይ የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ለሁሉም ሠልጣኞች የተሳትፎ ምስክር ወረቀትም ተበርክቷል፡፡

በሥልጠናው እንደተገለጸው ኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት/Entrepreneurship Development Institute (EDI) ለወጣቶች፣ ለሴቶች እና ለአመራር አካላት ቢዝነስ ተኮር የማማከር አገልግሎትና ሥልጠናዎችን የሚሰጥ መንግሥታዊ ተቋም ነው፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት