አርበ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ጋር በመተባበር ‹‹አርባ ምንጭ ታንብብ›› በሚል መሪ ቃል ከጥር 18-21/2016 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ከተማ የንባብ ሳምንት አካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ያሬድ ተፈራ በሀገራችን የንባብ ባህልን ለማሳደግ ትምህርት ቤቶች፣ የወጣቶች ማዕላት፣ የማረሚያ ቤቶችና የሕዝብ ቤተ መጻሕፍትን ለመደገፍና ለማጠናከር እንዲሁም የንባብ ክበባትን በመመሥረት የንባብ ባህልን ለማስፋት ታልሞ የንባብ ሳምንት መርሃ ግብር እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል፡፡ ተቋሙ በአርባ ምንጭና ጨንቻ ከተሞች ለሚገኙ የማረሚያ ቤቶችና የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት፣ የ2 ደረጃ ት/ቤቶች ቤተ መጻሕፍትና የወጣቶች ማእከላት 1,364,000 ብር ወጪ በማድረግ እንዲሁም ከዛጎል መጻሕፍት ባንክ ያገኛቸውን 200 መጻሕፍት አበርክቷል ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በዕውቀት፣ በክሂሎትና በቴክኖሎጂ ላይ የሚሠራ በመሆኑ መርሃ ግብሩ ከተቋሙ ዓላማዎች ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የንባብ ሳምንት ከዚህ ቀደም ሁለት ዙር መከናወኑን ያስታወሱት ፕሬዝደንቱ በመርሃ ግብሩ የቀረቡት የተደራጁ የመጻሕፍት ዝግጅቶች የተማሪዎችንና የከተማውን ወጣቶች የንባብ ፍላጎት የሚጨምሩና የንባብ ተሳትፎን የሚያሳድጉ ናቸው ብለዋል፡፡ የሚያነብ ዜጋ የተሻለ ግንዛቤ ይኖረዋል ያሉት ፕሬዝደንቱ የመርሃ ግብሩ ዓላማ ማንበብ የሚወድና አንብቦ ባገኘው ዕውቀት ራሱንና ሀገሩን የሚያሳድግ ዜጋ መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ መጻሕፍት ለሕይወት አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ንባብ አመለካከታችንን እንድናሰፋና ትርጉም ያለው ሕይውት እንድንመራ ይረዳናል ብለዋል፡፡ የዲጂታል ዘመን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እየተዳከመ የመጣውን የንባብ ባህል ለማሳደግ መሰል መርሃ ግብሮች አበርክቶ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

ደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ንባብን አስመልቶ ሲናገር በተለይ ወጣቶች በቀን ለ15 ደቂቃ መለስተኛ መጻሕፍትን በማንበብ ቢለማመዱ ንባብን የሕይወታቸው አንድ አካል ማድረግ ይችላሉ ብሏል፡፡ ደራሲ ዘነበ ንባብ ሀገርን የሚገነባና ሩቅ ተመልካች ዜጋ የሚፈጥር ትልቅ ጸጋ እንደሆነም ተናግሯል፡፡

በመርሃ ግብሩ ደራሲ ስንቅነህ እሸቱ ‹ባህልን፣ ቋንቋንና እሴትን እናንብብ› በሚል አጭር ንግግር ያደረገ ሲሆን ወጣት ጸሐፍት የግጥም ሥራቸውን አቅርበዋል፡፡ የመጻሕፍት ዐውደ ርእይ፣ የሥነ ጽሑፍ ምሽት፣ ዐውደ ውይይትና የመጻሕፍት ልገሳ የተካሄደ ሲሆን ለዩኒቨርሲቲው የቤተ መጻሕፍት፣ ሬጅስትራርና የሰው ሀብት ባለሙያዎች በሪከርድና ሰነድ አያያዝ ዙሪያ የግማሽ ቀን ሥልጠናም ተሰጥቷል፡፡

በዕለቱ በኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ባለሙያ አቶ እስራኤል በዙ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ለማኅበረሰብ ሁለንተናዊ እድገት፣ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመረጃ አገልግሎትና ቤተ መጻሕፍት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ሳሙኤል የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት አጠቃቀም ልምድ፣ በአቶ ታደለ ሙላት የተቀናጀ የቤተ መጻሕፍት ሥርዓት ቴክኖሎጂ እንዲሁም በዶ/ር ተመስገን ምንዋጋው ንባብና ቴክኖሎጂ የሚሉ የውይይት መነሻ ሰነዶች ቀርበዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት