የሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህሪ ሳይንስ ት/ቤት የባህሪ ማሻሻያ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከ“International Youth Fellowship” ጋር በመተባበር በአዕምሮ ውቅር (Mindset) ዙሪያ ከደቡብ ኮሪያ በመጡ አሠልጣኞች ለጫሞ ካምፓስና ለዋናው ግቢ 2 ዓመትና ከዚያ በላይ ተማሪዎች፣ ለመደበኛና ኢ-መደበኛ ሪሜዲያል ተማሪዎች እና ለባይራ አዳሪ 2ኛ ደ/ት/ቤት ተማሪዎች  ጥር 18/2016 ዓ/ም የአዕምሮ ውቅር/Mindset/ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

ሥልጠናው የአስተሳሰብ ለውጥ ለሀገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ፣ የአዕምሮ ውቅር አስፈላጊነትና ጥቅም፣ ደቡብ ኮሪያ ያደገችና ጠንካራ ሀገር እንድትሆን የአዕምሮ ውቅር አበርክቶ፣ ጠንካራ የአዕምሮ አስተሳሰብ ሥርዓትን በመገንባት ከባድ ነገሮችን ለማሸነፍ የአስተሳሰብ ለውጥ በማድረግ ንቃተ ህሊናንና የማሰብ ችሎታን ማዳበር የሚያስችሉ መሠረታዊ ጉዳዮችን በስፋት ዳስሷል፡፡

የምርምርና  ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ መሰጠቱን አስታውሰው የሰው አዕምሮ ለለውጥና የተፈለገውን ግብ ለማሳካት ወሳኝ መሣሪያ በመሆኑ በግል ያለንን አቅም ለማጎልበትም ሆነ በአከባቢያችን ያሉትን የሌሎች ሰዎችን ብቃት ከፍ ለማድረግ መሰል ሥልጠናዎች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ም/ፕሬዝደንቱ አክለውም ተማሪዎች ይህንን ሥልጠና መውሰዳቸው ለወደፊት ሕይወታቸው ስኬት እንደሚያግዛቸው፣ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዴት ማለፍና ወሳኝ ምላሾችን መስጠት እንዲሁም በትምህርታቸው ላይ ኃላፊነትን እንዲወስዱና ከፍ ያለ ጥረት በማድረግ የትምህርት ጉዟቸውን ውጤታማ እንዲያደርጉ የሚችሉበትን አቅም ይፈጥራል ጠቁመዋል፡፡

የሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህሪ ሳይንስ ት/ቤት ዲን አቶ አንለይ ብርሃኑ ከሀገራችን የሕዝብ ቁጥር ወጣቱ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዝ በመሆኑ በወጣቶች አስተሳሰብ ላይ መሥራት ተገቢና መሠረታዊ በመሆኑ ደቡብ ኮሪያ ያላትን የሥራ ልምድ ለመቅሰም ሥልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ አንለይ ሥልጠናው ወጣቱ ኃይል እንዲበረታታ፣ እንዲነቃቃና ጥሩ ራዕይ ኖሮት እንዲሠራ የሚያግዝና እንደ ግለሰብም ሰዎች እራሳቸውን የሚያበረቱበት፣ የሚያበቁበትና አሸናፊ የሚያደርጋቸውን አስተሳስብ የሚያዳብሩበት እንዲሁም ለሀገራቸው ሁለንተናዊ ዕድገት ከመንግሥት ጋር በቅንጅት የመሥራት ባህልን ለማዳበር የሚያስችል አስተሳሰብ የሚፈጥሩበት መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ሥልጠናው በቀጣይነት ለተለያዩ ክፍሎች ተደራሽ እንደሚደረግም ዲኑ ጠቁመዋል፡፡

አሠልጣኝና የ“International Youth Fellowship – Ethiopia Director & Mindset Specialist/ የኢንተርናሽናል ዩስ ፌለውሺፕ - ኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የማይንድሴት ስፔሻሊስት ዶ/ር ኪም ሂዩብ/Dr kim Hyub/ እንደገለጹት ተማሪዎች መጪውን የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማሳካት የሚማሩና ወደፊት ሀገራቸውንም የሚመሩ ዜጎች በመሆናቸው የተሻለ አስተሳሰብ እንዲያጎለብቱ ታልሞ ሥልጠናው እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ ግለሰብን ብሎም ሀገርን ለመለወጥ ፋይዳው ጉልህ በመሆኑ መሰል ሥልጠናዎችን በስፋት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር ኪም ተናግረዋል፡፡ እንደ አሠልጣኙ አገላለጽ ደቡብ ኮሪያን ከድኅነት ለማውጣትና ያደገችና ጠንካራ ሀገር እንድትሆን ያደረጋት በአዕምሮ ውቅር  ትምህርት የተገኘው የአስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ የሕዝብ ቁጥርና እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ሀገር በመሆኗ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቱን እንዴት መጠቀም እንደሚገባ ማወቅና  የመለወጥ አስተሳሰብን መያዝ እንዲቻል በአዕምሮ ውቅር ላይ መሠረት አድርጎ መሥራቱ አበርክቶው ከፍተኛ መሆኑን ዶ/ር ኪም አክለው ተናግረዋል፡፡ አሠልጣኙ ሠልጣኞች በሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች ሳይበገሩ ችግሮችን ወደ መልካም ዕድል በመለወጥ የተሳካ ሕይወት ለመኖርና ግባቸውን ለማሳካትም በብርታት እንዲሠሩ አሳስበዋል፡፡   

ሠልጣኞች በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ኢትዮጵያን እንዴት መቀየር እንደሚቻል፣ ደቡብ ኮሪያ በጥቂት ዓመታት ያደገችበትንና ጠንካራ ሀገር የሆነችበትን ልምድ፣ ጊዜና አቅምን እንዴት መጠቀም እንደሚገባና የሀብት አጠቃቀምን ለሀገር ዕድገትና ለቀጣይ ትውልድ በማሰብ እንዴት ማድረግ እንደሚቻል ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት