የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ለጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎረንሲክ ሜዲስንና ቶክሲኮሎጂ ስፔሻሊቲ ተማሪዎች ከታኅሣሥ 18 - ጥር 24/2016 ዓ/ም በሁለት ዙሮች የፎረንሲክ ናሙና ምርመራ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ጋር በትብብር ለመሥራት በተፈራረመው የሁለትዮሽ ውል ስምምነት መሠረት የፎረንሲክ ናሙና ምርመራ ሥልጠናው በሁለት ዙሮች የተሰጠ ሲሆን በ1 ዙር ስድስት እና በ2 ዙር ሦስት በአጠቃላይ ዘጠኝ የስፔሻሊቲ ተማሪዎች መሠልጠናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ ከዚህ ቀደም መሰል ሥልጠናዎችን ለማግኘት ሕንድ ሀገር ይኬድ የነበረ ሲሆን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ ቤተ ሙከራዎችን በዘመናዊ መሣሪያዎች በማደራጀቱ ሥልጠናውን እዚሁ በሀገር ውስጥ መስጠት ተችሏል ብለዋል፡፡ ይህም እንደ ሀገር ከፍተኛ ወጪን የሚቀንስ፣ የዩኒቨርሲቲውን ዕውቅና የሚጨምርና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ዶ/ር ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም በፎረንሲክ ዘርፍ የሚሠለጥኑ ሌሎች ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲያችን ቢመጡ በቂ የተግባር ልምድን ከሳይንሱ ጋር  ያጣመረ ሥልጠና የሚሰጥ መሆኑን ዲኑ ገልጸዋል፡፡

የኬሚስትሪ ት/ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ገዳሙ ሙላታ እንደገለጹት ቤተ ሙከራዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁና በዘመናዊ ቁሳቁሶች የተሟሉ በመሆኑ በተለይም ከወንጀል ምርመራ ጋር በተገናኘ ባለሙያዎችን በሥልጠና በማብቃት ኅብረተሰቡን ለማገልገል ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየሠራ ነው፡፡

የፎረንሲክ ኬሚስትሪና ቶክሲኮሎጂ መምህርና ተመራማሪ አሠልጣኝ ማሞ ድቃሙ በፎረንሲክ ሳይንስ ዘርፍ ስውር የጣት ዐሻራ፣ የሕክምና ሰነድ፣ የዛቻ ደብዳቤዎችና ሌሎች የተጠረጠሩ ሰነዶች፤ በፎረንሲክ ኬሚስትሪ ዘርፍ አደንዛዥ ዕፅና ሌሎች የተከለከሉ መድኃኒቶች፤ በፎረንሲክ ቶክሲኮሎጂ ዘርፍ የተመረዘ ምግብና መጠጥ፣ ተመርዘው ከሞቱና ከተጎዱ ሰዎች ደም፣ ሽንት፣ ጸጉር፣ ጉበት እና ከመሳሰሉ ላይ ናሙና በመውሰድ ዘመናዊ መሣሪያዎቹን ተጠቅሞ መመርመርን አስመልክቶ በሥልጠናው በስፋት ማየት አንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ ዘርፉ ለሀገር እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ መንግሥት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቂ ትኩረትና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም አሠልጣኙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ሠልጣኞች በነበራቸው ቆይታ ተግባራዊ ዕውቀት እንዳገኙ ገልጸው በቀጣይ ሥልጠናው ሲሰጥ ሰፊ ጊዜ ተወስዶ ቢሰጥ መልካም መሆኑን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት