በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አዘጋጅነት ከተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ለተወጣጡ የኮሌጁ መምህራንና ተመራማሪዎች ከጥር 23 - 26 ለአራት ተከታታይ ቀናት የጂአይኤስ አጠቃቀም ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ሥልጠናው በተለያዩ ቦታዎች ያሉ የበሽታ ስርጭቶችን ለመረዳት የሚያስችል የጂኦግራፊካል ኢንፎርሜሽን ሲስተም/GIS/ ሥልጠና በመሆኑ ምርምሮችን በመሥራት ላይ ለሚገኙ መምህራን የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ስለሆነም ተመራማሪዎች በበቂ ሁኔታና ቀለል ባለ መልኩ መረጃዎችን ማደራጀት እንዲችሉና ምርምሮችን በተሳካ ሁኔታ እንዲያከናውኑ እንደሚያግዛቸው ዶ/ር ደስታ ጠቁመዋል፡፡

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ረ/ፕ ምስጉን ሸዋንግዛው በኮሌጁ የተለያዩ የምርምር ፕሮጀክቶች እየተሠሩ እንደሚገኙ ገልጸው ፕሮጀክቶቹን ለማጠናከር  ከውጭ ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ በኮሌጁ በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ የሚታተሙ ምርምሮች እንዲጠናከሩና በተለይ በጂአይኤስ/GIS/ አጠቃቀም ላይ ግንዛቤያቸው እንዲያድግ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የበሽታ ስርጭቶችን ለመቆጣጠር እንዲቻል መሰል ሥልጠናዎችን ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው፡፡  

የኢትዮጵያ ጂአይኤስ ሶሳይቲ የአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ አስተባባሪና የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ የእንደስትሪ ትስስርና ማበልጸጊያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሀብተማርያም አጥናፍ ከዚህ ቀደም መሰል ሥልጠና ለደን ምርምር፣ ለተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ እንዲሁም ለዞኑ የግብርና ዘርፍ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ ሥልጠናውን እየወሰዱ የሚገኙት በአብዛኛው የ3 ዲግሪ ትምህርታቸውን በመማር ላይ ያሉ መምህራን ሲሆኑ ሥልጠናው ለሚሠሩት የፕሮጀክትና የምርምር ሥራዎች አስፈላጊና አጋዥ ነው፡፡ በተጨማሪም ሥልጠናው መምህራን ጂአይኤስን በመጠቀም እንዴት አድርገው ካርታ/Map/ ማዘጋጀት እንደሚችሉ፣ ጂፒኤስን/GPS/ን በመጠቀም ዳታዎችን እንዴት መውሰድ እንደሚችሉ፣ ወደ መስክ ያልወጡ የጂፒኤስ ዳታዎችን እንዴት ወደ ጂፒኤስ ሥርዓት ማስገባት እንደሚችሉ እንዲሁም ዳታዎችን እንዴት መፍጠር እንደሚችሉ እንደሚዳስስ አቶ ሀብተማርያም አብራርተዋል፡፡

ሥልጠናው ካተኮረባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል “GIS”፣ “GPS”፣ “Arc GIS interface”፣ “Basic Tools in GIS”፣ “Map Composition”፣ “Data creation in GIS”፣ Data input from GIS” እና “Use of GIS in mapping Health facilities and projects” የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሥልጠናውን ከማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ከጂኦግራፊና አካባቢያዊ ጥናት ትምህርት ክፍል የመጡ መምህራን ሰጥተዋል፡፡

ከሥልጠናው መጨረሻ ሥልጠናውን ተከታትለው ላጠናቀቁ ተሳታፊዎች የምሥክር ወረቀት ተበርክቷል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት