ዩኒቨርሲቲው ከአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የማንጎ ማውረጃ ቴክኖሎጂ ጥር 28/2016 ዓ/ም በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ኦቾሎ ላንቴ ቀበሌ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ለሙከራ አቅርቧል፡፡ የቴክኖሎጂዎቹን አጠቃቀም አስመልክቶ በባለሙያዎች ገለጻ በማድረግ ሁለት የማውረጃ መሣሪያዎችን በቡድን የተከፈሉ አርሶ አደሮች የተረከቡ ሲሆን ከአርሶ አደሩ የሚመጣውን ግብረ መልስ ተከትሎ ማሻሻያ ታክሎ በስፋት ለማዳረስ እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት መምህር አቶ ሳምሶን ኃይሉ የአጠቃቀም ሥልጠናውን ሲሰጡ እንዳብራሩት የማንጎ ማውረጃው ከብረት የተሠራ፣ እስከ 10 ሜትር ያህል በሚፈለገው መጠን የሚያጥርና የሚረዝም፣ ተነቃቃይና በቀላሉ የሚንቀሳቀስ እንዲሁም አውራጁ አንድ ቦታ ቆሞ 360 ዲግሪ አዟዙሮ ሊጠቀመው የሚችል ሲሆን ማንጎው ተበጥሶ የሚያርፍበት መረብ እስከ አምስት ኪሎ የሚይዝ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ማንጎን በመልቀም ሂደት የሚደርሱ አካላዊ ጉዳቶችን ለማስቀረት፣ የማንጎ ጥራትን ለማስጠበቅና ብክነትን ለመቀነስ የሚረዳ በመሆኑ ተጠቃሚው አርሶ አደር በሙከራ ሂደቱ የገጠሙትን ችግሮችና የማሻሻያ ሃሳቦች ግብረ መልስ ሲሰጥ ተገቢው ማስተካከያ ይደረግበታል ብለዋል፡፡

ቴክኖሎጂውን ያዘጋጁት ባለሙያዎች በአካባቢው ባደረጉት ቅድመ ዳሰሳ የማንጎ ምርትን በመሰብሰብ ሂደት ከፍተኛ የምርት ብክነትና የጥራት ጉድለት እንዳለ እንዲሁም ዛፉ ላይ ወጥተው በሚያወርዱበት ጊዜ መውደቅና እስከ ሕይወት ኅልፈት የሚደርስ ጉዳት እንደሚደርስባቸው ማየታቸው ቴክኖሎጂውን ለመፍጠር እንዳነሳሳቸው መምህር ሳምሶን ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ የማኅበረሰቡን ችግር በቴክኖሎጂ ለማቃለል ሃሳብ ይዘው ለሚመጡ የፕሮፖዛል ጥሪ የሚያደርግ ሲሆን ጥሪውን ተከትሎ የዩኒቨርሲቲው ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ እና የአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት መምህራን በመጣመር የማንጎ ማውረጃ ቴክኖሎጂ ፕሮፖዛሉን አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ወጪ በመሸፈን ሁለት የማንጎ ማውረጃዎች ተሠርተው ለሙከራ መቅረባቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት ም/ፕሬዝደንት ተ/ፕ በኃይሉ መርደኪዮስ ዩኒቨርሲቲው በላንቴና አካባቢው ማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎችን ሲሠራ መቆየቱን ጠቅሰው ለሙከራ የቀረበው ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲው የግብርና ምርትና ምርታማነትን ከማሻሻል አኳያ ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል፡፡ ቴክኖሎጂው የሙከራ ሂደቱን ሲያልፍ በማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት በኩል በሰፊው የማዳረስ ሥራ እንደሚሠራ ም/ፕሬዝደንቱ ጠቁመዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት ም/ዲን አቶ ወርቅነህ ኃ/ሚካኤል ኢንስቲትዩቱ በጥናትና ምርምር ታግዞ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠርና በማላመድ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ከአጋር አካላት ጋር እንደሚሠራ አስታውሰው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም የጋራ ስምምነት አድርጎ ከሚሠራባቸው ተቋማት አንዱ ነው ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲውና ኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ለሙከራ የቀረበውን ቴክኖሎጂ ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ በማዳረስም ሆነ ሌሎች በአካባቢው አስፈላጊ የሆኑ መሰል ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ የጋራ ሥራው ቀጣይነት እንደሚኖረው ም/ዲኑ ተናግረዋል፡፡

የማንጎ ማውረጃ ቴክኖሎጂውን ለሙከራ የተረከቡት አርሶ አደሮች በአካባቢው ማንጎ በባህላዊው መንገድ ሲለቀም ያለውን ችግር አውስተው ተቋማቱ ችግራቸውን ለማቃለል ቴክኖሎጂውን ይዘው በመቅረባቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በአካባቢው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የማንጎ ዛፎቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቃና ምርት አልባ እያደረገ የሚገኘውን የማንጎ ተክል በሽታ ለማስወገድ ዩኒቨርሲቲው የዕውቀት ቤት እንደ መሆኑ ትኩረት አድርጎ መፍትሔ እንዲያፈላልግ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት