የአርባ ምንጭ የኒቨርሲቲ የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ለጫሞ፣ ዓባያና ሳውላ ካምፓሶች አዲስ ገቢ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ዲስፕሊን መመሪያ ላይ ከጥር 25 - የካቲት 02/2016 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

ሥልጠናው የሥነ ምግባር ጽንሰ ሃሳብ፣ የሥነ ምግባር መርሆዎች፣ የሥነ ምግባር ግድፈቶችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ዲስፕሊን መመሪያ ላይ ያተኮረ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው የሥነ ዜጋ ት/ክፍል መምህራን ዶ/ር ያሲን ሁሴን እና መ/ር ግርማ መንግሥቱ ተሰጥቷል፡፡

የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ እታፈራሁ መኮንን እንደተናገሩት ሥልጠናው በየዓመቱ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የሚሰጥ ሲሆን ተማሪዎች መብትና ግዴታዎቻቸውን በአግባቡ ተረድተው በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ተግባራዊ እንዲያደርጉት ግንዛቤ የሚፈጥር ነው፡፡ ተማሪዎች የመጡለትን ዓላማ ቀዳሚ በማድረግ በተቋሙ የሚሰጠውን አገልግሎት በእኩልነትና ፍትሐዊነት የመጠቀም መብት መኖሩን ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲሁም በትምህርት ዓለምም ሆነ ከተመረቁ በኋላ በሥነ ምግባር የታነጹ ዜጎች እንዲሆኑ ሥልጠናው መዘጋጀቱን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ ብርሃኑ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች በየጊዜው የሚሰጡ ሥልጠናዎች ተማሪዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚፈጽሙትን የዲስፕሊን ጥሰት ለመከላከል ጥቅም እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የተማሪዎችን የትምህርት ጊዜ ማዕከል በማድረግ ሥነ ምግባርና ክሂሎት የሚያዳብሩ ሥልጠናዎችን በየክፍሉ በመስጠት ተማሪዎችን ውጤታማ ማድረግ ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር መስፍን መንዛ በበኩላቸው ተማሪዎች ተግተው በመሥራት ጥሩ ውጤት ከማስመዝገብ ባሻገር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲስፕሊን መመሪያና የመመሪያው ጥሰት ሊያስከትል የሚችለውን ቅጣት ለይተው ማወቅ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ ሙስናን ከፈተና ማስኮረጅ ጀምሮ በመከላከል ተማሪዎች በሥነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ  መሰል ሥልጠናዎች አስፈላጊነታቸው የጎላ መሆኑንም ዲኑ ተናግረዋል፡፡

የሳውላ ካምፓስ የአስተዳደር ጉዳዮች ዳይሬክተርና የካምፓስ ኃላፊው ተወካይ መ/ር ዘለቀ ዶሳ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የሥነ ምግባር ሥልጠና መሰጠቱ ከመምህራን፣ ከአስተዳደር ሠራተኞችና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በጥሩ ተግባቦት እንዲቆዩ እንዲሁም የንብረት አጠቃቀምን ጨምሮ የተስተካከለ የአመለካከት ለውጥ እንዲኖራቸው ሥልጠናው መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡

ሠልጣኝ ተማሪዎች በአስተያየቶቻቸው መብትና ግዴታቸውን አውቀው ከመምህራንና ከአስተዳደር ሠራተኞች ጋር በጋራ በመሥራት ለተሻለ ውጤት እንዲተጉ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት