መቀመጫውን ስዊድን ሀገር ያደረገው ሂዩማን ብሪጅ /HUMAN BRiDGE የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታልን የካቲት 01/2016 ዓ/ም ጎብኝተዋል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ደስታ ጋልቻ ለጎብኚዎች በሰጡት ገለጻ እንዳመላከቱት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር ከስድስት መቶ በላይ አልጋዎች እንደሚኖሩትና ከሰባት ሚሊየን በላይ ለሚሆን የአካባቢው ማኅበረሰብ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዶ/ር ደስታ አሁን ላይ ሆስፒታሉን በቅርብ ጊዜ ውስጥ በከፊል ሥራ ለማስጀመር የሚረዱ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ሆስፒታሉን በሕክምና ቁሳቁስ የማሟላት ሥራ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ደስታ በመንግሥት በጀት ከተፈጸሙ ግዢዎች ባሻገር ሂውማን ብሪጅ በሁለት ዙር ያደረገው ድጋፍ ለሆስፒታሉ እዚህ ደረጃ መድረስ የጎላ ሚና የተጫወተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ድርጅቱ እስከ አሁን ላደረገው ድጋፍ በዩኒቨርሲቲው ስም ያላቸውን ልባዊ ምስጋናና አድናቆት አቅርበዋል፡፡ ሆስፒታሉን ሙሉ በሙሉ በሕክምና ቁሳቁስ ማሟላት ከፍተኛ ገንዘብና የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃል ያሉት ዶ/ር ደስታ ከዚህ አንጻር ሂዩማን ብሪጅ ያደረገው ድጋፍ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑንና ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥያቄያቸውን ለሥራ ኃላፈዎቹ አቅርበዋል፡፡

የሂዩማን ብሪጅ ሊቀመንበር ቦ ጉልድስትራን/ Bo Guldstrand/ በበኩላቸው ድርጅታቸው በሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ላይ በማተኮር የሚሠራ ግብረ ሠናይ ድርጅት ሲሆን ከስዊድን ሆስፒታሎች እና የባዮሜዲካል ተቋማት ጋር በመገናኘት ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ያገለገሉ ነገር ግን በጥሩ ሁኔታ የሚሠሩ መሣሪያዎች በዓለም ዙሪያ ባሉ ሀገራት ለሚገኙ የሕክምና ተቋማት እያቀረበ ይገኛል ብለዋል፡፡ ድርጅታቸው ከዚህ ቀደም ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል የቁሳቁስ ድጋፎች ማድረጉን ያስታወሱት ሊቀመንበሩ ሆስፒታሉ የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁም የተደረጉ የቁሳቁስ ድጋፎች ያሉበትን ሁኔታና አስተዋጽኦ ለመመልከት ጉብኝቱ መደረጉን አውስተዋል፡፡ በጉብኝታቸው ለሆስፒታሉ ድጋፍ የተደረጉ ቁሳቁሶች ለአገልግሎት ዝግጁ እየተደረጉ መሆናቸውን እንዳረጋገጡ የገለጹት ሊቀመንበሩ ከሆስፒታሉ ግዙፍነት አንጻር  በቀጣይ ተጨማሪ ድጋፎችን ለማድረግ ተቋማቸው እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

ሂዩማን ብሪጅ ከዚህ ቀደም ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል የሚውሉ ዘመናዊና በሪሞት የሚሠሩ የታካሚና የቀዶ ጥገና ክፍል አልጋዎች፣ ፍራሾች፣ ዊልቸሮች፣ ክራንቾች፣ የቀዶ ጥገና ክፍል መብራቶች፣ ስትሬቸር፣ የላቦራቶሪ ወንበሮች፣ የሕፃናት ማሞቂያዎች፣ የሕክምና አልባሳትና ሌሎች ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት