አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ክርስቲያን ኤይድ/Christian Aid/ እና ሶስ ሳህል /SOS Sahel Ethiopia/ ከተሰኙ ግብር ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ከተለያዩ ዞኖች ለተወጣጡ ማኅበራት ተወካዮችና ሥራ አጥ ወጣቶች ለ10 ቀናት የሚቆይ  የአሠልጣኞች ሥልጠና ከጥር 29/2016 ዓ/ም ጀምሮ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሥልጠናው የእንሰት ተረፈ ምርት ከሆነው ቃጫ ዕሴት የተጨመረባቸውና የተሻለ ዋጋ የሚያወጡ ጌጣጌጦችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ማምረት የሚያስችል ነው፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ቴክኖሎጂ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የእንሰት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር አዲሱ ፈቃዱ እንደገለጹት የእንሰት ቃጫ በባህላዊ መንገድ ከሚሠሩ ቁሳቁሶችና ለጂፕሰም ቦርድ መሥሪያነት ለሽያጭ ከመቅረቡ ባሻገር ለሌላ አገልግሎት አይውልም፡፡ ከቃጫ ዕሴት ተጨምሮባቸው የተሻለ ዋጋ የሚያወጡና ለቤትና ለቢሮ ጌጣጌጥ እንዲሁም ለዕለት ከዕለት አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን ማምረት እንደሚቻል የተናገሩት ዶ/ር አዲሱ ወጣቶቹ የቁሳቁሶቹን አሠራር በቂ ክሂሎት አግኝተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ የሥልጠናው ዋና ዓላማ ነው፡፡ በዘርፉ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻል የሥልጠናው ሌላኛው ዓላማ ሲሆን አካባቢው ከፍተኛ የቱሪስት ፍስት ያለው እንደመሆኑ ቱሪስቶችን ማዕከል ያደረጉ ምርቶችን ወጣቶች አምርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ ማድረግም ሌላኛው የሥልጠናው ትኩረት መሆኑን ዶ/ር አዲሱ ጠቁመዋል፡፡

ከሥልጠናው በኋላ ለሠልጣኞች ለሥራው የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን በመስጠት በቀጥታ ወደ ምርትና ሌሎችን ወደ ማሠልጠን እንዲገቡ እንደሚደረግ የጠቀሱት ዶ/ር አዲሱ መስኩ ለብዙ ሺህ ሥራ አጥ ወጣቶች አዲስ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ያለው በመሆኑ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር መሥራት ለሚፈልጉ መንግሥታዊና  መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች የአብረን እንሥራ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

ከአሠልጣኞች መካከል ከጉራጌ ዞን ጌታ ወረዳ የመጡት ወ/ሮ አመቱ ተዘራ ከዚህ ቀደም ይህንን ሥልጠና በጃፓኑ ጃይካ አማካኝት የወሰዱ መሆናቸውንና አሁን ላይ ከ80 የአካባቢው ሴቶች ጋር በማኅበር በመደራጀት ከቃጫ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ አመቱ ገለፃ ከዚህ ቀደም ምንም ዕሴት ሳይጨመር ጥሬ ቃጫ ለገበያ በማቅረብ አነስተኛ ገቢ ያገኙ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን ከቃጫ ቦርሳ፣ ዘምቢል፣ የአበባ ማስቀመጫ፣ የፍራፍሬ ማቅረቢያና ሌሎች ቁሳቁሶች ሠርተው ለገበያ በማቅረብ በእጅጉ የተሻለና ኑሯቸውን የቀየረ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ አመቱ በሥልጠናው እየተሳተፉ ለሚገኙ ወጣቶች ከቃጫ የተለያዩ ጌጣጌጦችንና ቁሳቁሶችን ማምረት እንዲችሉ እየተደረገ ሲሆን ሠልጣኞችም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ምርቶችን ማምረት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ አመቱ መስኩ በእጅጉ አዋጭና ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት ያለበት መሆኑን በተግባር የታየ በመሆኑ ወጣቶቹ ከሥልጠናው በኋላ ቀጥታ ወደ ሥራ በመግባት የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ለመቀየር እንዲተጉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከወላይታ ዞን ዳሞት ቡላሳ ወረዳ የመጣችው ሠልጣኝ ዘላለም አባተ በቃጫ ሥራ ላይ በማኅበር ተደራጅተው እየሠሩ ቢሆንም ከቃጫ ገመድ ከመሥራትና በጥሬው ከመሸጥ ባሻገር በዚህ መልክ በርካታ ቁሳቁሶች ይሠሩበታል ብላ አስባ እንደማታውቅ ተናግራለች፡፡  ከወላይታ ሶዶ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በኮንስትራክሽን የትምህርት መስክ በደረጃ V መመረቋን የምትገልጸው ወጣት ዘላለም በሥልጠናው ከቃጫ ዘምቢል፣ ቦርሳ፣ መሶብ፣ ቀበቶ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ማምረት እንደሚቻልና ይህንንም በተግባር ማየቷን ገልፃለች፡፡ ይህንን ሥልጠና ላዘጋጁ አካላት ምሥጋና ያቀረበችው ወጣት ዘላለም ከሥልጠናው መልስ ሌሎች የማኅበራቸውን አባላት በማሠልጠን በዘርፉ ላይ ውጤታማ ለመሆን ዝግጁ መሆኗንም ተናግራለች፡፡

ከጋሞ ዞን ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዶርዜ ሆሎኦ ቀበሌ የመጣችው ሌላኛዋ ሠልጣኝ ፍቅርተ አበራ በበኩሏ ከቃጫ በእጅጉ ውብ የሆኑ ጌታጌጦችና የቤት ውስጥ ዕቃዎች ተሠርተው ማየቷና በተግባር መሥራቷ በእጅጉ እንዳስገረማት እንዲሁም ይህንን የመሰለ በዓይነቱ የተለየ ሥልጠና የማግኘት ዕድል ማግኘቷ በእጅጉ እንዳስደሳት ተናግራለች፡፡ ዶርዜና አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የቱሪስት ፍሰት ያለበት አካባቢ በመሆኑ ከሥልጠናው መልስ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሆን ለቱሪስቶች የሚሆኑ ጌጣጌቶችን ከቃጫ በማምረት ለሽያጭ ለማቅረብ ከወዲሁ ማቀዷን ተናግራለች፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት