አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከኮንሶ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ጋር በመተባበር በሰብአዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ እንዲሁም በሰላም እሴት ግንባታ ዙሪያ በኮንሶ ዞን ለሚገኙ 250 የፖሊስ አባላት ከየካቲት 6-9/2016 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ የማኅበረሰብ ጉድኝት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ መ/ር መሐመድ ሹሬ እንደገለጹት የሥልጠናው ዓላማ በተጠርጣሪዎችና ታራሚዎች መብትና ግዴታ እንዲሁም እንዴት ሊያዙ እና ሊስተናገዱ እንደሚገባ ለዞኑ ፖሊስ አባላት ግንዛቤ መፍጠርና ማነቃቃት ብሎም በሥራ ሂደት የሚስተዋሉ ግድፈቶች ካሉ ማጥራትና ማረም ነው፡፡ የሥልጠናው ሂደት ችግሮችን በማንሳትና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማሳየት ሳይንሳዊና ሀገር በቀል በሆነ መንገድ ለመማማር የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኮንሶ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ለሚታ ጉራሾ በአሁኑ ሰዓት ለዜጎች አስፈላጊ ከሚባሉት ጉዳዮች ዋነኛው የሰብአዊ መብት ጉዳይ በመሆኑ የፖሊስ አባላቱ ለሥልጠናው ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሥልጠናው የሚገኘውን ግብአት ተግባራዊ ማድረግና ለሌሎችም ማዳረስ ይገባል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የሥልጠና ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ምላሽ በመስጠቱ አመስግነው ዩኒቨርሲቲው በቅርበት የሚገኝ እንደመሆኑ  በቀጣይ ሌሎች መሰል ድጋፎችን እንዲያደርግላቸውም ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ሠልጣኝ ፖሊሶች በትምህርትና ሥልጠና ያገኙትን ዕውቀት ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በማዛመድ በችግሮች ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የማኅበረሰቡን ሀገር በቀል ግጭት የማስወገድ ሥርዓት ከማስቀጠል አንጻርም ይበልጥ ሊሠራበት እንደሚገባ ዶ/ር ተክሉ አሳስበዋል፡፡

ሰብአዊ መብት ለሰላምና ለልማት ያለውን ሚና አስመልክቶ ሥልጠና የሰጡት የዩኒቨርሲቲው የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ት/ክፍል መመምህር አቶ መዝገቡ ማንደፍሮ እንደገለጹት ሰብአዊ መብቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የተቆራኙና ከተፈጥሯዊ ሰብአዊ ባህርይ የሚመነጩ በመሆናቸው ለሁሉም የሰው ልጆች በእኩል መከበር ያለባቸው ሲሆን ግለሰቦችም ሆኑ መንግሥት ሰብአዊ መብትን ማክበርና ማስከበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሠልጣኙ በሰብአዊ መብት ጥሰት እና ጣልቃ ገብነት መካከል ያለውን ልዩነት በሰፊው ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ሰብአዊ መብትን በመገደብና ባለመገደብ የሚመጣውን ውጤት በማወዳደር ፖሊስ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መምህር አቶ ምንዳ ወንድሙ በበኩላቸው ሰብአዊ መብት በኢትዮጵያ በሚል ሥልጠና የሰጡ ሲሆን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጾች በአመዛኙ ትኩረት ያደረጉት በሰብአዊ መብት አዋጆች ላይ መሆኑ ሕገ መንግሥቱ ለሰብአዊ መብቶች የሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ፖሊሶች የሕግ አስፈጻሚ እንደመሆናቸው ለሰብአዊ መብት መጣስም ሆነ መከበር ቅርብ በመሆናቸው የዜጎች መብት እንዲከበር የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ መ/ር ምንዳ ተናግረዋል፡፡

የሰብአዊ መብት መለያ ባህርያት፣ ጠቀሜታና እንዲከበሩ መደረግ ያለባቸው ጉዳዮች እንዲሁም የፖሊስ ሚና በሥልጠናው ትኩረት ከተደረገባቸው ርእሰ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የኮንሶ ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሰለሞን ጋማይዳ የዜጎችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሁም የሀገሪቱን ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ማክበርና ማስከበር፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሕዝቦችን ደኅንነት መጠበቅ እንዲሁም ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ በምርመራ በማጣራት ለሚመለከተው አካል በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ማስከበር የፖሊስ ዋና ተልእኮ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ተልእኮ አፈጻጸም ሂደት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ክፍተቱን ለመሙላት ሥልጠናው አቅማቸውን ይበልጥ እንደሚያጎለብት ተናግረዋል፡፡   

የኮንሶ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ፣ የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዥና የዞንና የወረዳ ፖሊሶች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሥልጠናው መክፈቻ ላይ ተገኝተዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት