የጋሞ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንደስትሪ መምሪያ የጫሞ ሐይቅ ረግረጋማ ስፍራን/Buffer Zone/ መልሶ ለማልማትና ለመጠበቅ የሚያስችል 1.65 ሄክታር ተጨማሪ መሬት ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ /AMU-IUC/፣ ጋንታ አባ እና ባይራ ለተሰኙ ማኅበራት የካቲት 08/2016 ዓ/ም አስረክቧል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የጋሞ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንደስትሪ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ግርማ እንደገለጹት መምሪያው ለጋንታ አባ የፍራፍሬና አትክልት እንዲሁም ለባይራ የከብት ድለባ የግል ማኅበራት የኢንቨስትመንት መሬት የሰጠ ሲሆን ማኅበራቱ ከተሰጣቸው የኢንቨስትመንት መሬት ጎን ለጎን የሐይቁ ዳርቻ /Buffer Zone/ የሆነውን 1.65 ሄክታር መሬት ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ /AMU-IUC/ ፕራግራም ጋር በመተባበር እንዲያለሙት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በሐይቁ ዙሪያ የሚገኘውን ረግረጋማ ስፍራ መጠበቅ ባለመቻሉ በሐይቁ ላይም ሆነ በዙሪያው ባሉ የእርሻ መሬቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የገለጹት አቶ ሳሙኤል መምሪያው ለኢንቨስትመንት ያዘጋጀው 11 ሄክታር የሚሆን መሬት በሐይቁ መዋጡን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከሌቶ የዓሣ አስጋሪዎች ማኅበር ጋር በመሆን በወሰደው ሦስት ሄክታር ረግረጋማ መሬት ላይ እያከናወነ የሚገኘው የመልሶ ማልማትና ጥበቃ ሥራ የሚበረታታና ጥሩ ልምዶች የተገኙበት ሲሆን ሥራውን በሁለቱም ሐይቆች ዙሪያ ለማስፋፋት የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ በትኩረትና በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የAMU-IUC ፕሮግራም ማኔጀርና የውኃ ሥነ ምኅዳር ተመራማሪ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ ዩኒቨርሲቲው ከሮማንና ኃይለማርያም ፋውንዴሽን፣ አይ.ዩ.ሲ/IUC/፣ ኬ.ዩ. ሊውቨን/KU Leuven/፣ ቦስ+/BOSS+/፣ ኢንባር/INBAR/፣ ጋሞ ዞንና ከሌቶ ዓሣ አስጋሪዎች ማኅበር ጋር በመሆን ሦስት ሄክታር የሚሆን የጫሞ ሐይቅ ረግረጋማ ስፍራ ከዞኑ በመረከብ ምርምር ላይ የተመሠረቱ የመልሶ ማልማት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ ዶ/ር ፋሲል በስፍራው በሰው ጫና ምክንያት የጠፉ ዕፅዋትን በመትከልና በመንከባከብ እንዲሁም አካባቢውን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ እንዲሆን በማድረግ ቦታውን ወደነበረበት መመለስ እየተቻለ ሲሆን በዚህም  ማኅበሩ የተሻለ የዓሣ ምርት እያገኘ ከመሆኑ ባሻገር በአካባቢው ጠፍተው የነበሩ አዕዋፍና ሌሎች እንስሳት እየታዩ ነው ብለዋል፡፡ ከረግረጋማ ቦታ ዕፅዋት ባሻገር ጥናትን መሠረት ያደረጉ ለከብት መኖነት የሚውሉ ዕፅዋት በስፍራው ተተክለው እየለሙ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ፋሲል በዚህም የማኅበሩ አባላት ፍየሎችን በማርባት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ፋሲል በስፍራው የታዩ ለውጦችና እመርታዎች አሁን በትብብር እንድናለማ ከዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንደስትሪ መምሪያ ያለምንም ማመንታት ተጨማሪ መሬት እንዲሰጠን የበኩሉን ሚና ተወጥቷል ብለዋል፡፡

የሐይቁን ረግረጋማ ስፍራ በመለየት የሚከናወኑ የመልሶ ማልማትና ጥበቃ ሥራዎች በሐይቁ ላይ እየደረሱ የሚገኙ አሁናዊ አደጋዎችንና ስጋቶችን ከመቅረፍ አንጻር ወሳኝ በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲው እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከዞኑ በተሰጠው መሬት ከማኅበራቱ ጋር በመተባበር የመልሶ ማልማትና ጥበቃ ሥራ እንደሚሠራ ዶ/ር ፋሲል ተናግረዋል፡፡ በሐይቁ ዙሪያ እስከ 50 ሜትር የሚገኘው ረግረጋማ ስፍራ ሙሉ በሙሉ ሊለማና ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ያሉት ዶ/ር ፋሲል በቀጣይ በሐይቁ ዙሪያ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ቦታውን በማልማታቸው ሊያገኙት በሚችሉት ጠቀሜታ ላይ ግንዛቤ በመፍጠር በትብብር ለመሥራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጋንታ አባ የአትክልትና ፍራፍሬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ቆንጬ ዎልታ ከጋሞ ዞን የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል አንዱ የጫሞ ሐይቅ እንደመሆኑ ሐይቁን ከአደጋ የመታደግ ጉዳይ የጋራ ሥራ ነው ብለዋል፡፡ በሐይቁ ዙሪያ የሚገኘውን ረግረጋማ ስፍራ መጠበቅና ማልማት ጠቀሜታው ለሐይቁ ብቻ ሳይሆን ለራሳቸውም ጭምር እንደሆነ ግንዛቤ እንዳለቸው የገለጹት ባለሀብቱ በቀጣይ በጋራ የተሰጣቸውን የሐይቅ ዳርቻ ከዩኒቨርሲቲው በሚሰጣቸው ሳይንሳዊ ምክረ ሃሳብ ላይ ተመሥርተው ለማልማትና ለመጠበቅ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

ረግረጋማ መሬቱን ከዚህ ቀደም ወደ ነበረበት መመለስና እንደ ደንገል፣ ፊላና ሶኬ ባሉ የረግረጋማ አካባቢ ዕፅዋት መሸፈን በዋናናት ደለልና በካይ ንጥረ ነገሮች ከተፋሰሱ ወደ ሐይቁ እንዳይገቡ የማጣራትና የመከላከል ሥራ ይሠራል፡፡ ከዚህም ባሻገር ስፍራው ለዓሣ፣ ለአዕዋፍና ለሌሎች የውኃ ውስጥ እንስሳት የመመገቢያ፣ የመራቢያና የመኖሪያ ቦታ በመሆን የሚያገለግል እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ በሐይቅ ተፋሰስ ላይ ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው ይህንን የሐይቅ ክፍል በተቻለ መጠን መጠበቅና መልሶ ማልማት ወሳኝ በመሆኑ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኩል የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎችን ለማስፋት የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተውና ተቀናጅተው ሊሠሩ ይገባል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት