በውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ሦስት ፕሮጀክቶች የደረሱበት ደረጃ የመጀመሪያ ዙር ግምገማ የካቲት 08/2016 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

‹‹Rehabilitation of Irrigation infrastructures and Demonstration of modern irrigation at Gamo Zone, Kola Shara››፣ ‹‹Adoptation of Best Irrigation Water Management at Daramalo Woreda Gamo Zone, Ethiopia›› እና ‹‹Training overview on Decision Support System Agrotechnology Transfer (DSSAT)›› ግምገማ የተካሄደባቸው ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

በኢንስቲትዩቱ የማኅበረሰብ ጉድኝት ዘርፍ የማኅበረሰቡን ችግር የሚቀርፉ ሦስት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን ግምገማው ፕሮጀክቶቹ የደረሱበት ደረጃና የገጠማቸው ችግር ላይ በመወያየት በቀጣይ ጊዜያት በትጋት ሠርቶ ከፍጻሜ ለማድረስ የተዘጋጀ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ቦጋለ ገ/ማርያም ገልጸዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ማኅበረሰብ ጉድኝት አስተባባሪ መ/ርት ፍቅርተ ሥዩም እንደተናገሩት ከፕሮጀክቱ አንደኛው በቆላ ሻራ ቀደም ሲል የነበረን የመስኖ መስመር ማኅበረሰቡን በማስተባበር ጠግኖ ለአገልግሎት ማብቃት ሲሆን ሁለተኛው  በዳራማሎ ወረዳ በአርሶ አደሩ ዘንድ ያለውን ‹‹የተሻለ ምርት ለማግኘት ብዙ ውኃ መጠቀም ያስፈልጋል›› የሚል አመለካከት ለማስቀየርና የተሻለ የመስኖ ውኃ አጠቃቀምን ለማኅበረሰቡ በማሳየት የውኃ ሀብትን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማድረግ የሚሠራ ነው፡፡ ሦስተኛው ፕሮጀክት የሥልጠና ፕሮጀክት ነው ያሉት አስተባባሪዋ የሥልጠናው ይዘት፣ ለማን እንደሚሰጥና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ታይተዋል ብለዋል፡፡

የውኃ ሀብትና መስኖ ምኅንድስና ፋከልቲ መምህርና የፕሮጀክቱ ተሳታፊ መ/ር ሰልማን ሀሰን በዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ በማኅበረሰብ ተሳትፎ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ገልጸው ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን እንዲቀርጹ ለመምህራን በቀረበው ጥሪ መሠረት በቆላ ሻራ የሀሬ ወንዝን ማኅበረሰቡ በአግባቡ አለመጠቀሙን፣ የመስኖ ቦዮች በደለል መሞላታቸውንና የውኃ አከፋፈል ለምርቱ በቂ አለመሆኑን በማየት አካባቢውን መርጠው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡ በመጀመሪያው ዙር አካባቢውን ማጽዳት፣ የቅየሳ ሥራ፣ መረጃ መሰብሰብ፣ ከቦይ ውስጥ ደለሉን ማስወገድ እንዲሁም ለምርቱ ምን ያህል ውኃ እንደሚበቃ ዘመናዊና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማኅበረሰቡ ማሳወቅ ሥራዎች መከናወናቸውን መ/ር ሰልማን ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት