‹‹የዘመኑ ከተሞች ለኢትዮጵያ ብልጽግና›› በሚል መሪ ቃል በወላይታ ሶዶ ከተማ ከየካቲት 09-15/2016 ዓ/ም በተዘጋጀው 9ው የከተሞች ፎረም አርባ ምንጭ ከተማን በመደገፍ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተሳታፊ ሆኗል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

በፎረሙ 124 ከተሞች የተሳተፉ ሲሆን የከተሞችን እድገት ለማፋጠን፣ ከተሞች ያሉበትን የእድገት ደረጃ ለማስተዋወቅና ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ ልምድ ለመቀመር ያግዛል ተብሏል፡፡ በፎረሙ በተካሄደ ዐውደ ርእይ የተለያዩ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች፣ የኢንደስትሪ ውጤቶች እንዲሁም ከተሞቹ ያሉበት የእድገትና ኢኮኖሚ ደረጃ በተለያዩ ሁነቶች የቀረበ ሲሆን የፓናል ውይይቶችም ተካሂደዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተሠሩ ችግር ፈቺ የእንሰት ቴክኖሎጂዎች፣ ከእንሰት ቃጫ የተሠሩ ጌጣጌጦች፣ በዩኒቨርሲቲው አርክቴክቶች የቀረቡ የተመረጡ ቦታዎች ሞዴል ዲዛይኖች፣ የማዕድን ጥናት ውጤቶች፣ በአርባ ምንጭ ከተማ ያሉ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ማሳያ፣ ከሙዝ ግንድ ቃጫ ማውጫና የእንሰት መኖ ማከማቻ ማሽን፣ የሙዝ ዱቄትና ከሙዝ የተቀናበሩ ምርቶች፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ ባህላዊ ቤቶችና መብሎች፣ የሞሪንጋ ምርቶችና ባህላዊ ጭፈራዎች ቀርበዋል፡፡

የኢፌዴሪ ም/ጠ/ሚኒስትርና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከተሞችን ለነዋሪው ምቹና ተስማሚ ለማድረግና ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር የታለመውን ብልጽግና ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የከተሞች መልማት ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለኢንደስትሪ መስፋፋት፣ ለሕዝቦች ትስስርና ኅብረ ብሄራዊነትን ለማጎልበት ይረዳል ያሉት ም/ጠ/ሚኒስትሩ የመሠረተ ልማት መስፋፋት ለከተሞች እድገት መፋጠን ጉልህ ድርሻ ያለው በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መሥራት አለባቸው ብለዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከተሞች እርስ በእርስ የሚተዋወቁበት፣ ተሞክሮ የሚለዋወጡበት፣ በጎ ፉክክር የሚያደርጉበትና አብሮ የመሥራት ባህል የሚያዳብሩበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ጊዜያት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ድህነትን ለመቀነስ ጠንክረው መሥራት እንደሚገባቸውም ሚኒስትሯ አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በማኅበረሰብ ተኮር ሥራዎች ዩኒቨርሲቲውና ከተማው በቅንጅት እንደሚሠሩ ገልጸው በውድድሩ የቀረቡት የአደባባይ ዲዛይን፣ የአርክቴክቸር ሥራዎችና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲው ከከተማው ልማታዊ ሥራዎች ጎን ለመሆኑ ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡ በቀጣይም የከተማውን ሥራዎች በቴክኖሎጂ ማዘመንና የከተማውን ግንባታ ዲዛይን ከማስዋብ ጋር ተያያዥ ሥራዎች ላይ ዩኒቨርሲቲው ከከተማው ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲውን ወክለው በፎረሙ የተገኙት የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ከከተማው በቀረበው ጥሪ መሠረት ከተማውንና ዩኒቨርሲቲውን ለማስተዋወቅ የሚረዱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ እሴት የተጨመረባቸው ምግቦችና ሌሎችም በዩኒቨርሲቲውና በፕሮጀክት ተደግፈው የተሠሩ ተግባራት ለእይታና ለሽያጭ መቅረባቸውን ገልጸዋል። ዶ/ር ቶሌራ አክለውም መድረኩ ያለንን ያስተዋወቅንበት፣ የአቀራረብ ልምድ የቀሰምንበትና ለቀጣይ ሥራዎች ግብአት ያገኘንበት በመሆኑ በቀጣይ ከከተማው ጋር በቅንጅት በመሥራት በተሻለ አቀራረብ ለመገኘት ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

የዝግጅቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በተመለከቷቸው ነገሮች መደሰታቸውን ገልጸው ሁሉም የየራሱን ባህል፣ ትውፊትና እሴቶች ይዞ በመቅረቡ በአንድ ቦታ ላይ ሙሉ ኢትዮጵያን ማየት የቻልንበት መድረክ ነው ብለዋል። መርሃ ግብሩ አካባቢውን ከማስተዋወቅ ባሻገር ሕዝብን ከህዝብ ለማስተሳሰር ላቅ ያለ ሚና ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።

በፎረሙ ም/ጠ/ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እና ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ የየከተሞች አስተዳዳሪዎችና ከንቲባዎች እንዲሁም በርካታ ተጋባዥ እንግዶች የተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ 10ው የከተሞች ፎረም በሰመራ ከተማ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCCD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት