የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለ113 በሀገራችን ለ48 ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ‹‹ሴቶችን እናብቃ፤ ልማትና ሰላምን እናረጋግጥ›› በሚል መሪ ቃል የካቲት 27/2016 ዓ/ም አክብሯል፡፡ ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት በዓሉ በዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ እንደሚከበር አስታውሰው በዩኒቨርሲቲያችን ያሉ ሴቶች ተሳትፎና ውጤታማነት ጋር ተያይዞ በኃላፊነትም ሆነ በባለሙያ ደረጃ እንዲሁም በተማሪዎች በኩል ያለውን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በመግለጽ ሃሳብና አስተያየት የሚሰጥበት፣ የምንማማርበትና ለውጥ የምናመጣበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡

የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህሌ በዓሉ የሚከበርበት ዋነኛ ዓላማ በዓለም ያሉ መንግሥታት የሴቶች ጉዳይ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ጉዳይ እንደሆነ አምነው በመቀበል በሴቶች ዙሪያ ፖሊሲዎቻቸውን፣ ሕጎቻቸውንና አሠራሮቻቸውን በመፈተሽ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ አድልኦዎችን እንዲያስወግዱና የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጡ ማነሳሳት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ በዓሉ ለእኩልነት፣ ሰላምና እድገት ሴቶች ያደረጉትን ተጋድሎ የሚዘክር ሲሆን ለአንድነትና ተቀናጅቶ ለለውጥ ለመንቀሳቀስ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ ዳይሬክተሯ ያለፉት ሴቶች ያከናወኑትን ገድሎች ከመዘከር በዘለለ በዩኒቨርሲቲው ለሴቶች ምቹ የሥራና የመማሪያ አካባቢ በመፍጠር፣ በያለንበት የትምህርትና የሥራ ክፍል የሚታዩ ጾታዊ ጥቃቶችን በመከላከልና በማስቆም፣ ሴት ተማሪዎች ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲወጡና መልካም ሥነ ምግባር እንዲላበሱ በመደገፍ፣ ከእኛ በታች ያሉ ተማሪዎችን በዕውቀትና በክሂሎት ከፍ እንዲሉ በመሥራት፣ ምርምሮቻችን የሴቶችን ጉዳይ ያካተቱ በማድረግና ማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ሴቶችን ችግሮች በመለየት መፍትሔ በማፈላለግ እንዲሁም አድሎአዊ አሠራሮች ሲታዩ ሕግን ተከትሎ በማስቆም የድርሻችንን ማበርከት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

‹‹የሴቶች ትግል እና ያመጡት ለውጥ ከዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ተሞክሮዎች አንጻር›› በሚል ርእስ ዕለቱን የሚመለከት ሰነድ ያቀረቡት መምህርት ሠናይት አስፋው የሴቶች ቀን ከሚከርበት ምክንያቶች መካከል ሴቶች ላይ በተለያየ መልኩ የሚፈጸሙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጭቆናዎች ዋና ዋና መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዜጎች መብቶቻቸው እንዲከበሩ በተለያዩ ሀገራት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ጉዳዩን አስመልክቶ በሕገ መንግሥቱና በልዩ ልዩ ሕጎች አንቀጾችን እንዲካተቱ በማድረግ በርካታ ሴቶች እልህ አስጨራሽ ትግሎችን ማድረጋቸውን መ/ርት ሠናይት ተናግረዋል፡፡

በፕሮግራሙ  ግጥም፣ መነባነብ እንዲሁም ዕለቱን የሚመለከት ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/

ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university

ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/

ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት