ከአሜሪካን ሀገር ኮሎራዶ ስቴት/Colorado State/ ዩኒቨርሲቲ የመጡት የግብርና ኤክስቴንሽን መ/ርና ተመራማሪ ፕ/ር አሰፋ ገብረአምላክ በማኅበረሰብ ጉድኝት፣ በዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትሰስር እንዲሁም በተዛማጅ ምርምሮች ዙሪያ ተሞክሮን ትኩረት ያደረገ ሥልጠና የካቲት 25/2016 ዓ/ም ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ሰጥተዋል፡፡ተጨማሪ ፎቶዎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክታቸው እንደገለጹት ‹‹ጤናማ ሰው መሆን ከራስ አልፎ ለሌሎች መኖር›› በመሆኑ የፕሮፌሰሩ መምጣት በውጪው ዓለምና በሀገር ውስጥ ያለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበረሰብ ተኮር አገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ ምን እንደሚመስል ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡  

ፕሮፌሰር አሰፋ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሻሻል ተገቢነትና ተጠያቂነት የሰፈነ ምላሽ መስጠት፣ ውጤታማ የመማር ማስተማር ሥርዓተ ትምህርት መቅረፅ፣ የማኅበረሰቡን ፍላጎቶች ትኩረት ያደረጉ የምርምር ሥራዎችን መሥራትና የማኅበረሰብ ጉድኝት ተግባራትን ማከናወን እንዲሁም የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን መፍታት የሚችሉ በቂ ዕውቀትና ክሂሎት ያላቸው  ተማሪዎችን ለማፍራት በሀገረ አሜሪካ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ በ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራት ያለው የትምህርት አሠጣጥ አለመኖር፣ ውጤታማና ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ ሥርዓተ-ትምህርቶችን አለመቅረጽ፣ የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች የማኅበረሰቡን ችግር ትኩረት ያደረጉ አለመሆን እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ገንዘብ ለጋሽ ድርጅት አድርጎ መመልከት እና ከልማዳዊ የአሠራር ሥርዓት አለመውጣት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚስተዋሉ ተግዳሮቶች መካከል ተጠቃሾች መሆናቸውን ፕሮፌሰሩ አመላክተዋል፡፡

ያለ ትስስር በዓለምና ሀገር አቀፍ ደረጃ ለውጥ ማምጣት አይቻልም ያሉት ፕ/ር አሰፋ ትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች የትምህርት አመራር አካላት ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዲሁም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የእርስ በእርስ ትስስር በመፍጠር ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት መሻሻል የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ አክለውም ተማሪዎችን በንቃት ተሳታፊ የሚያደርግና የማኅበረሰቡን ችግር ለመለየትና ለመፍታት የሚያስችል፣ አቅም የሚፈጥር እና ከመማር ማስተማሩ ጋር የተጣመረ የአሠራር ሂደትን መከተል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የምርምር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሀ/ማርያም እንደገለጹት ሥልጠናው ከመማር ማስተማሩ ሂደት ባሻገር በምርምርና ማኅበረሰብ ጉድኝት እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስር ዘርፎች ላይ ያላቸውን ሙያዊ ዕውቀትና ክሂሎት ማካፈልን ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡   

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ
የብሩህ ተስፋ ማዕከል!

ለተጨማሪ መረጃ በድረ-ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን ይከተሉን፡-

ድረ-ገጽ - https://www.amu.edu.et/
ቴሌግራም - https://t.me/arbaminch_university
ፌስቡክ - https://www.facebook.com/ArbaMinchUniversityCAD/
ዩቲዩብ - https://www.youtube.com/channel/UCOO_nclhMo8M3r74OyPBlVA

የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት